በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የዕቅድ አስፈላጊነት

መግቢያ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ድካሙን ብዙ ውጤቱን ጥቂት የሚያድረግ ምስቅልቅልን እየፈጠረ ያለው በእቅድ፣ በበጀት፣ በፕላንና በሪፖርት አለመመራት ነው።

እግዚአሔር ለዘላለማዊ ዕቅዱ ሰውን ነው የፈጠረው ሌላው ሁሉ ሐላፊ ጠፊ ነው። ሰው በእግዚአሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ጉልህ ሱታፌ ስላለው በዕቅድና በሪፖርት መመራት አለበት፤ ካለዚያማ ከእንስሳት በምን ይለያል። «የሩቅ መቶ ዓመት ዕቅድ ካለህ ሰው ትከል፣ የአሥር ዓመት ዕቅድ ካለህ ዛፍ ትከል የአንድ ዓመት ዕቅድ ካለህ ሩዝ ትከል» የቻይኖች አባባል።
ቃለ ዓዋዲው በቅጡ ከሥራ ላይ አልዋለም። በአስተዳደር በኩል ቤተ ክርስቲያናችን ቀጭጫ ቀርታለች። ከላይ ከተጠቀሱት አስፈላጊ ነገሮች ረፖርት የሚባለው ለስሙ አለ። ይሁን እንጂ በርእይ፣ በእቅድና በበጀት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት ለማግኘት አዳጋች ነው። በሠለጠነ መንገድ መሥራት፣ ማስተዳደርና መምራት ገና ይቀረናል።

አሁን በመላ ኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ካህናትና ምእመናን በጋራ የሚያስቀምጧቸው የተሰማሙባቸው ለተግባራዊነታቸውም በትጋትና በብቃት የሚሳተፉባቸው ዓላማዎችና ግቦች አዘጋጅታ መንቀሳቀስና ውዝፍ ሥራዎቿን ሁሉ ለማካካስ ወገቧን አጥብቃ መነሣት አለባት።

ይህንም ለማዘጋጀት በጮሌዎች፣ በባለዘመኖች፣ በባለዘመዶች፣ በባለገንዘቦች ተገፍተው ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኗን ሊቃውንት ማቅረብ፣ በሁለቱም በዘመናዊውም በሀገረ በቀሉ የአብነት ትምህርትም የተሳሉ ልጆቿን መጋበዝ፣ በነጻ እንዲያገለግሏት መጠየቅ፣ ካህናትንና ምእመናንን ያሳተፈ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ በሠለጠነው እና ዓለም አሁን በደረሰበት የአሠራር ደረጃ ስትለካ በዚህ ረገድ ባሳለፈቻቸው የሃይማኖት አልባ ሥርዓቶች ተፅዕኖ ምክንያት የራሷም ድክመት ተጨምሮበት ችግር ይታይባታልና ዕቅድና በጀትን፣ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ሪፖርትን፣ ግቦችና መሪ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ቅድሚያ ልትሰጥ ይገባል።

ዕቅድ ምንድ ነው?

የርእይ ትንሽ ወንድም ሊባል ይችላል። ርእይ የአምስት አመት ከዚያም በላይ የሚወስድ ሊሆን ይችላል ዕቅድ ግን የሩብ ዓመት፣የ2ኛ ሩብ ዓመት፣ የሦስተኛ ሩብ ዓመት፣ የዓራተኛ ሩብ ዓመት ብሎ የዓመቱን ዕቅድ አስቸኳ፣ ቅድሚያ ቀጣይ ሥራዎችን መድቦና ቅደም ተከተል ሰጥቶ የሚተገበር ስለሆነ የቅርብ ጊዜ የወደፊት እንቅስቃሴ መግለጫ፣ መሄጃ መንገድ፣ አሁን ካለንበት ተነሥተን ለመድረስ ካሰብንበት መድርሻ መንገድና የትኩረት አቅጣጫ ሊባል ይችላል።

ብዙ ጊዜ ስለ ዕቅድ ስናነብ፣ ስንማር እና ስንሰማ ሁሉም ሰው ዕቅድ እንዳለው እንገነዘባለን። ዕቅድ አለህ ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ ሁሉም ሰው አዎ ነው የሚል። ነገር ግን ከሁለተኛው ጥያቄ ላይ በልበ ሙሉነት አዎ ሲል የሚገኝ በጣም ጥቂት ሰው ነው። ይኸውም ታዲያ ወደግራም ወደቀኝም ሳትል አትኩረህና ቀጥ ብለህ እየሄድክበት ነው? ሲሉት ምክንያት የሚደረድር ብዙ ነው። እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎች ማለትም ታዲያ ዕቅድህን ቤተሰብ ተስማምቶበታል? ገልጽ ነው? ሊተገበር የሚችል ነው? ሲሉት ዝም የሚለው ይበዛል። ስለዚህ እቅድ ቢያንስ የሚከተሉትን ነጥቦች ማሟላት ወይም መሆን አለበት፦

ግልጽ፦ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ተረድተውት የሚተጉለት ፍጻሜውን ለማየት ከሥራ ሠዓት በላይ እንኳ ቢድክሙ የማይሰማቸው በልቡናቸው ውስጥ የሠረፃቸው ለምን እንደዚያ እንደሚያደርጉም ለሚጠይቃቸው ሁሉ ማስረዳት የሚችሉት።

በአጋሮች ከስምምነት የተደረሰበት፦ ዕቅድ ከቤት ይጀምራል። ቤተ ሰቡ ከሰፋ በመላ ቤተሰቡ የተደገፈ መሆን አለበት። ያለዚያ ከትዳር አጋር ከሚስት ጋር መመካከርና በዕቅዱ መስማማት ያስፈልጋል። «እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት» (ዘፍ. 2፥18)፡፡ ባል በዕቅዱ ውስጥ ረዳት ሁና የተሰጠችውን የትዳር ጓድኛውን ካላስገባትና ካላማከራት ዕንቅፋት መሆኗ የማይቀር ነው፡፡ ዝም ብትል እንኳ ትብብሯ በጣም የመነመነ ስለሚሆን ትጎትተዋለች፡፡ «ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች» (ምሳ.14፥1)። እንደተባለው ቤተሰቧን ደግፋ የምትይዝ ምሰሶ ከመሆኗም በላይ፣ ታታሪነቷ ለቤተሰቡ መልካም አርአያነት አለውና የራሷ በቤቱ የወደፊት ሁኔታ ግልጽ እይታ ሊኖራት ይገባል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከሆነች ወይም ሌላ ድርጅት ደግሞ ሁሉም የባለ ድርሻ አካላት ያጸደቁትና የተስማሙበት ሊሆን ይገባል።

ሊተገበር የሚችል፦ ዕቅድ ሊተገበር የሚችል መሆን እንዳለበት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው አምጥተን እናስረዳለን።
  ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? (ሉቃ 14፥28-31)።

ተብሎ እንደተነገረ ለአንድ ቋሚና ስም የሚያስጠራ ሥራ ለመሥራት በዕቅድ መንቀሳቀስ ዕቅዱም ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ሁሉ ማሟላት እንዳለበት ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ብርሃን ሆኖ ያሳያል። ይህ አንቀጽ እቅድ ሊተገበር የሚችል መሆን እንዳለበት ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በላቀ ሁኔታ ስለ ባጀት ያስተምራል።

በጊዜ የተወሰነ መሆን /Time bound፦ ሥራችንን ጧት፣ ማታ፣ ቀን፣ ዘንድሮ ከርሞ ወዘተ መቼ መሥራት አለብን የሚለውን እንድናስብ በምሳሌነት የሚያስተምሩን ጥቃቅን ፍጥረታት እናገኛለን

«ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ» (ምሳ. 30፥25)።

በጊዜ የተወሰነ መሆን አለበት የሚለውንና በበጋ መኗቸውን ይሰበስባሉ የሚለውን አዛምዶ ማየት ማስተዋልም ያስፈልጋል። እነዚህ ጉንዳኖች ጥቃቅን ፍጥረታት ናቸው ነገር ግን ጥበበኞችና በዕቅድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ምግባቸውን በበጋ ካላከማቹ ሁለት መጥፎ ነገሮችን ይጋፈጣሉ። ወይ ዝናብ ከማይደርስበት ጉድጓዳቸው ውስጥ በረሀብ ይሞታሉ ወይም ምግብ ፈለጋ ያለ ወቅቱና ሠዓቱ ወጥተው በጎርፍ ይወሰዳሉ ወይም በከብት ከጭቃ ጋር ይዳጣሉ። ሥራውን በየትኛው ጊዜ ማከናወን እንዳለበት የማይለይ ሰውም እንዲሁ ነው።

ከዚህ ላይ ደግሞ ልብ ሊባል የሚገባው ዕቅድ ፕላን አለመሆኑ ነው። በርካታ ሰዎች እቅድና ፕላንን ያምታታሉ ወይንም አንድ አድርገው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ልዩነት አላቸው። እቅድ መድረሻ ሲሆን ፕላን ከግቡ ለመድረስ የምንጠቀምበት ጥበብ፣ ብልኻት፣ ስልትና ዘዴ ነው።

ዕቅድን በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የሚረዱ ጠቃሚ ነገሮች

ዕቅድን በተሳካ ሁኔታ ለማሳካት የሚረዱ ተከታታይነት ያላቸው በርካታ ስልቶችና ብልሃቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን የከተል ይጠቅማል።

በጀት

ዕቅድን ለመተግበር አስፈላጊ የሆነው ነገር በጄት ነው። ርእይ፣ እቅድና በጄት የተባሉት የአስተዳደር ቁልፎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምብዛም የማይወደዱ በአብዛኛውም የማይሠራባቸው ነገር ግን በግድ መተግበር ያለባቸው ናቸው። በወንጌልም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም እያንዳንዱ መምሪያ በዕቅድና በበጀት እንዲመራ የተሠራና የተቀመጠ ቢሆንም ቃለ ዓዋዲው በተግባር ባለመዋሉ ምክንያት በየቤተ ክርስቲያኑ መተማመንን አጉድሏል፣ የጠብና ጭቅጭቅ መነሻም እየሆነ ይገኛል።

በእቅድና በበጄት መኖር ለድርጅት ብቻ ሳይሆን ለግል ኑሮም ጠቃሚ ነው። በበጃት መኖር ለአፍሪካ በተለይም ደመወዙን ተቀብሎ ወዲያው ከጓድኞቹ ጋር በመጠጣት፣ ወይም ያላሰበውን አንድ አንገብጋቢ ያልሆነ ነገር ሲያልፍ ስላየው ብቻ ድንገት ግዝቶበት ባዶ እጁን ወደቤቱ በመግባት ሚስቱንና ልጆቹን ሲያሳቅቅ ምንም ለማይመስለው ኢትዮጵያዊ ስለበጀት ማውራት ብዙም ጥቅም ላይሰጥ ይችላል። ይሁን አንጂ ወገንን ባለው አቅም ደስ ብሎት እንዲኖር ለመርዳትም ተደጋጋሚ ጥረት መደረግ አለበት።

የተቋም/ድርጅት በጀት እንደ ምሳሌ

Picture

ይህ የበጀት ዕቅድ ምሳሌ ልቅም ተደርጎ የተሠራ እንከን የለሽ ባይሆንም ሥርዓተ በጀትን ለመተግበር ለሚከብዳቸው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እንደመነሻ ሊያገለግል ይችላል።

እንደምሳሌ በቀረበው የላይኛው ሠንጠረዥ በገቢዎችም ይሁን በወጪዎች ላይ ከአምናው የሚጭምር ወይም የሚቀንስ ወይም በቀጥታ ያንኑ ያምናውን ብናይ ዘንድሮ የአምናውን ያህል የማያስወጡን ወይም የሚያስጨምሩን ወይም ያንኑ የአምናውን እንዳለ ሊፈጁ የሚችሉ የቀጣይ ዓመት ክንውኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው።

ይህ በጄት ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብር ሊኖረው ይገባል። ሥራዎችም አስቸኳይ የሆኑት፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ ተከታይ የሆኑት፣ እንደ አስፈላጊነታቸው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት፣ የሁለተኛ ሩብ ዓመት፣የሦስተኛ ሩብ ዓመት፣ የዐራተኛ ሩብ ዓመት ተብለው እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ ባለማቋረጥ የሚሠሩት ሥራዎች በዝርዝር ተለይተው የሰው ኃይል ተመድቦላቸው፣ ከላይ በተጠቀሱት የጊዜ ገደብ ተወስነው፣ መከናዎን መቻል አለባቸው።

ተስፋ

እቅድን ከግቡ ለማድረስ ከበጀት ቀጥሎ የሚያስፈልገ ተስፋ ነው። ተስፋ ትርጉሙ «አለኝታ፣ እምነት፣ አገኛለሁ ማለት፣ ወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ የሚነግር፣ የሚያበሥር፣ አይዞህ የሚል፣ የሚያስታምን፣ጸጋ ሀብት (የኪዳነ ወ/ክ/መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመ/ቃ/ሐዲስ፣ ገጽ. 879) ፡፡ ማለት ነው።

ተስፋ የሚጠቅም በጥበብ መንፈሳዊ ወይም በመዳን ረገድ ለእምነት ሰዎች፤ በሥራና በትምህርት በአጠቃላይ በጠበብ ሥጋዊ መሥመርም ለባለ ራእዮች ነው። ከአላማ፣ ከግብ፣ ከራእይ አጠገብ ቆሞ የሚጠቅሥ፤ ከዚህ ግብ ዘንድ መድረስ ትችላለህ ታገኛለህ እያለ ከሩቅ የሚጣራ፤ አንድ ዓመት፣ ሦስት ዓመት፣ አምስት ዓመት፣ አሥር ዓመት ወደፊት ቀድሞ ከሮጠ በኋላ ፊቱን ወደ በለራእዩና ባለራእዋ አዙሮ ሁል ጊዜ በየዕለቱ በርታ በርቺ የዛሬ … ዓመት ከእኔ አጠገብ ካለው መድረሻህ መድረሻሽ ትደርሳለህ፣ ትደርሻለሽ፣ ትደርሳላችሁ የሚል ብሥራት ዘወትር የሚያሰማ ለልብ ልብ የሚሰጥ ጸጋ ነው፡፡ ተስፋ ባይኖር ኖሮ ገበሬ አያርስም፣ ነጋዴ አይነግድም ወታደር አይዋጋም ነበር ተማሪም አይማርም ነበር በሽተኛም ባልዳነ ይልቁንም የዓለም ህዝብ እርስ በርሱ ተባልቶ ያልቅና ዓለም ባድማ ትሆን ነበር፡፡

አሁን ግን እነዚህ ሁሉ ወንዙን እየደለደሉ፣ ተራራውን እየናዱ፣ ጎድጓዳውን እየሞሉ፣ ‹‹አብጅ›› በሚለው ቋሚ መለኮታዊ ቡራኬ እየታገዙ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓለምን በማበጀትና ምቹ አስደሳች እንድትሆን ለማድረግ በተስፋ በመንቀሣቀሣቸው በርካታ ውጤቶችና ስኬቶች ተገኝተዋል፡፡

እምነት የሌለው ሰው ተሰፋ የለውም፤ ተስፋ መቁረጥ በራስ ላይ በቤተሰብ ላይ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ቀውሥ ከፍተኛ ነው፡፡ ተስፋ ቢስነት የተጠናወተው ሰው የመዳን ተስፋ የሌለው ሰይጣን የሚፈጽመውን ግፍና በደል የሚፈጽም አፍራሽ የሰይጣን ግብረ አበር ይሆናል፡፡

በእግዚአብሔር ማመን

በሃይማኖት በእምነት አያሌ ድንቆችና ተአምራት ወመንክራት እንደተደረጉ ተመዝግቦ በቅዱሳት መጻሕፍት እናገኛለን። በተቃራኒው እንደነ ቻርለስ ዳርዊን፣ ማርክስና ሌኒን ያሉት ከሀዲዎችና ያስካዷቸው አካላት እና በጣዖት የሚያምልኩ ማኅበረሰቦች ደግሞ ሲጠፉ ሲደመሰሱ፣ ሲበተኑ በጥንትም በአሁንም ዘመን ተመዝግቧል እያየንም ነው። «ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» (ማር.9፥23) ተብሎ በጌታችን፣ እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። (ዕብ.11፥1) ሲል ከማርክስና ከቻርለስ ዳርዊን እጅግ የሚበልጠው ቅዱሱ ሐዋርያ ጳውሎስ፣ ክህደታችውን ያፈራርስባቸውል። ተስፋ በእምነት የምትጨበጥ የሰው ልጆች ጥቅም መኋኗንም ያውጅባቸዋል። ይህ የሚታየው ዓለም ከሆነ ነገር በጊዜ ብዛት እራሱን እየለወጠ መጣ የሚለውን ፍልስፍናቸውንም ዓለማት ካለመኖር በእግዚአብሔር ሥልጣን ወደ መኖር የመጡ እንጂ የሚታይ መነሻ እንደሌላቸው ያስረግጥባቸዋል።

የጋራ ወይም የቡድን ሥራ

ትላልቅ ሥራዎችን ለማሳካት ድርጅት ወሳኝ ነው። ድርጅቶችም የቡድኖች ስብስብ ናቸው። «ድርጅት የጋራ ዓላማና ግቦች ባሏቸው ለዓላማቸውና ግቦቻቸው መሳካት እያንዳንዳቸው የሚያበረክቱት ነገር መኖሩን ባወቁ እና የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች የተገነባ ስብሰብ ነው» (ታደሰ ዶ/ር፣ 2006፣ገጽ 119)።፡አንድ ድርጅት የሰው፣ የገንዘብ፣ የእውቀት ሀብት፣ ያላቸው ሰዎች የሚፈጥሩት የጋራ እንቅስቃሴ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ኀያልነት የሃምሳ ስቴቶች ትብብርና አንድነት ውጤት ነው። በመተባበራቸውና በመሠልጠናቸው በርካታ ጥንታውያን ሀገሮች እያሉ ትናንት የተወለደችው አሜሪካ ይኸው ዓለምን ትገዛለች። ዩናይትድ ኪንግደም /እንግልጣር/ ኢንግላንድ ዋናው ሆኖ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ እነዚህ ከ1699 ጅምሮ አንድነታቸውን በመመሥረትና በማጠናከር አድገው እስከ አሁን ታላቋ ብሪታኒያ ለመባል ቻሉ።

የአውርፓ ኅብረት የት እንደደረሰ በኢሮ እንኳ መረዳት ይቻላል ወደፊትም ህብረቱን በሺታ ካላገኝው በጋራ እንደሚገኑና እንደሚጠቀሙ አያጠራጥርም። አንድነት መቼም ቢሆን ሲጠቅም እንጂ ሲጎዳ ታይቶ አያውቅም።

የጋራ ሥራ ምሳሌዎች

የጋራ ሥራ ዋጋ ያለውና ለዕድገትና ለልማት የተመረጠ ነው። በዱሳት መጻሕፍት የተመሰገነ ነው። ጥበብ 4:9-12፤ መዝ. 132:1። በተጨማሪ የሚከተሉትን ዋኖቻችንን መመልከት መቻን ከመቃተት ከሰው ጋር ለመሥራት ያነሳሳሉ፤

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

አብሮ ስለመሥራትና ሰው ስለመፍጠር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋናው አብነታችን ነው። 12 ሐዋርያት 72 አርድእት 36 ቅዱሳት አንስት በድምሩ 120 ቤተሰብ አደራጅቶ አብሮ መሥራትን መሥራቷል። «ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው» (ሉቃ.10፥1)። የሚለውም አስቀድሞ ሥራውን ቀጥሎም ሠራተኛውን መፍጠሩን እንዲሁም የውጤቱን አስደሳችነት ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን የምንማርበት ምሳሌ ነው።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ሥርዓት በአስተዳደር አቅጣጫ ብዙ ባይባልላትም በአብነት ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ወርሳዋለች። ከየአብነት ት/ቤቶቿ እውቀትን የሚቀስሙ ልጆቿ የነጻ ትምህርት ከሚሰጣችው ህዝበ ክርስቲያን ዘንድ ጧት ወይም ማታ ሂደው «በእንተ ስማ ለማርያም ስለ እመ ብርሃን ስለ ቸሩ እግዚአብሔር» የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ የድንግል ማርያምን እመ ብርሃንነት አውጀው ሰብከው የሰጧቸውን ተቀብለው፣ የሚመለሱ አርድእትን ሁል ጊዜ በየዕለቱ ጧትና ማታ ሁለት ሁለት እያደረገች ወደየመንደሩ ትልካለች። በአስተዳደር ሥራውና በአገልግሎቱም ይህንን በምሳሌነት ልትከተለው ይገባል።

ቅዱስ ጳውሎስ

ከጌታ ቀጥሎ አብሮና ተባብሮ ስለ መሥራት አግልጋይ ስለማፍራት ቅዱስ ጳውሎስን የመሰለ አርአያ ሐዋርያ አይገኝም። የስኬታማ አገልጋዮችንና መሪዎችን ታሪክ ስናጠና ብቻቸውን ከመምራት ይልቅ ከግዚአብሔር ጋር ሲሠሩና እና ብቁ የሆኑ አጋዦችን በማፍራትና ከጎናቸው በማድረግ በጋራ ሲጓዙ ውጤታማ ሲሆኑ እናያለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ያፋጠነው ብቻውን ሆኖ አይደለም፡፡ ከሁለት አስፈላጊ አካላት ጋር አብሮ በመሥራት ነው። እነሱም እግዚአብሔር እና ሰዎች ናቸው በግብረ ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን እጅግ የሚመስጥ ኅብረት እናያለን

«ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን፦ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው›› (የሐ/ሥ.18፥9)።

እግዚአብሔር ወልድ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር እንደነበረና አይዞህ ሲለው እንዴት ደስ ይላል። የማይለወጥ አምላክ እንደመሆኑ ለዛሬዎቹም የቅዱስ ጳውሎስ ተተኪዎችና የአገልግሎቱና የመንበሩ ወራሾች ኀይልና ጽናት የሚሆን ክፍል ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ከሰዎች ጋር በመሥራትና አገልጋዮችን አፍርቶ አብቅቶ አገልግሎትን በማፋጠንና በማስፋፋት በማዳረስ የሚተካከልው ሐዋርያ አልተገኘምና ትልቅ አርአያችነና ምሳሌያችን ነው። በሐዋርያዊ ሥራው የተባበሩትን እና በመከራው ጊዜ ያልተለዩትን የአግልግሎት አጋሮቹንና የመንፈስ ልጆቹን ባመሰገነበት አንድ አንቀጽ ብቻ እንኳ የተጠቀሱትን ቅዱሳን ብዛት ለማየት ታላቅ ቡድን እንደገነባና እንደነበረው እንረዳለን። ቀጥለን እንመልከት

‹‹በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት። በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም … በጌታ እጅግ ለደከመች ለተወደደች ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ››(ሮሜ. 16፥1-12)፡፡

የሚለውን በሮሜ መልእክቱ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ብቻ እንኳ የተቀመጠውን ማስረጃ ስናይ እነዚህና ሌሎችም ሁሉ አብረው ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጋር በመሥራት ነው ከሌሎቹ ሐዋርያት የበለጠ ውጤታማ የሆነ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ካፈራቸውና በአገልግሎት ካሰማራቸውና ከሾማቸው አርድእት ጥቂቶቹ

Picture

እንግዲህ ከላይ በጥቂቱ እንዳየነው አብሮና ተባብሮ መሥራት ሰውም ማፍራት አስፈላጊና መ/ቅዱሳዊመሆኑን ነው።

እቅድና ለነገ አትበሉ እንዴት ይስማማሉ?

ዮሴፍ የግብፅ ባለ ውለታ የሆነው የ14 ዓመት ዕቅድ አውጥቶ የሚንቀሳቀስ የእግዚአብሔር ሰው በመሆኑ ነው። በሰባት ዓመት የጥጋብ ዘመን ያከማቸውን ጥሪት ለሰባት ዓመት የረሀብ ዘመን በማብቃቃት ግብፅንና በአቅራቢያው የነበረውን ሕዝብ ከጥፋት የታደገ የመፍትሔና የዕቅድ ሰው ነው።

የመዳን ቀን ግን ዛሬም አይደለም አሁን ነው። ለመዳን ዕቅድ ማውጣት እንደማይቻል በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። (2ኛ ቆሮ. 6፥2) ተብሎ ተነግሯል። አሁን የተግባር ሠዓት እንጂ የዕቅድ ሠዓት አይደለምና።

በመንፈሳዊ መንገድ የአጭር ጊዜ የረጅም ጊዜ መካከለኛ የሚባል ነገር የለም ምክንያቱም የመዳን ቀን ዛሬ ሳይሆን አሁን ስለሆነ ነው፡፡

እንግዲህ በዘመናዊ አስተዳደር ከላይ የተገለጹት የሐውርያት አሠራር ርእይ፣ ዕቅድ፣ በጀት፣ የእቅድ አፈጻጸም ዝርዝር መርሐ ግብር፣ የሰው ሀብት ወይም ከሰው ጋር አብሮ መሥራት፣ ሪፖርት ተስፋ በእግዚአብሔር ማመን የተባሉት እና የመሳሰሉት ቁልፍ ክንውኖች አስተዳደርን ዘመናዊና ውጤታማ ያደርጉታል ተብሎ ይታመናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።

አባ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ።