ነገረ ጾም

ጾም ማለት ለተወሰኑ ዕለታት ሳምንታ ወይም ወራት ከእሕል ከውኃ መከልከል ነው። ሥጋን ከሚገነቡና የሥጋን ፍላጎት ከሚያጠናክሩ ከፍተኛ ኃይልና ሙቀት ከሚሰጡና ገንቢነት ካላቸው መብልና መጠጥ መከልከል፤ የሥጋ ፍላጎትን በማድከም፣ ሥጋዊ ሕይወት ለመንፈሳዊ ሕይወት እንዲታዘዝ ማድረግ ማለት ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እም መብልእ በጊዜ እውቅ- ፈቂዶ ኪያሁ ከመያድክም ኃይለ ፍትወት ወትትአዘዝ ለነፍስ ነባቢት እንዲል ጾም ከጸሎት ጋር የምትፈጸም በጸሎት ማሰሪያነት የምትከናወን መንፈሳዊ እቃጦር ናት። ነቢዩ ኢዮኤል አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ኢዮኤል ፪፥፲፪ እንዳለው ጾም ወደ እግዚአብሔር መመለሻ አንድዋ መንፈሳዊ መንገድ ናት። ጾም በሥጋዊ የዕለተዕለት ኑሮአችን እንኳ ከሰይጣን ፈተና ለመጠበቅ ትልቅ ፋይዳ አለው። ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ አስተምሮታል። አንድ ልጁ አጋንንት ያደረበትን ሰው ደቀ መዛሙርቱ ያድኑለት ዘንድ ጠይቆ ነብር በጊዜው አልተሳካም። ይህም እግዚአብሔር የጾምን ኃይል ሊያስተምራቸው ፈልጎ ነው።
ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት። ክርስቶስም ሲመልስ ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው። ማቴ ፲፯፥፲፱–፳፪ በመሆኑም ጾም ከሰይጣን ቁራኝነት የምንላቀቅባት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባት የነፍሳችን ቁስል የምትፈወስበት መድኃኒት ናት። ቅዱስ ያሬድም በምኩራብ ጾመ ድጓ እስመ ጾም በቁኤት ባቲ እሕታ ለሰላም ነጽር ላእሌነ አቡነ ክርስቶስ ለዘ በእንቲአነ መጦከ ነፍሰከ ጾም ልጓም ፍሬሃ ጥዑም እንዲሁም በመጽሐፈ መነኮሳት ጾምሰ እማ ለጸሎት ወእሕታ ለአርምሞ ወነቅዕ ለኩሉ ምግባረ ሰናይ የጸሎት እናት ጾም ናት፣የዝምታ እህትም ጾም ናት፣የበጎ ምግባር ሁሉ ምንጭም ጾም ናት በማለት የጾምን ታላቅነት ያስተምራሉ።
ጾም ሁለት ክፍሎች አሉት እነሱም
፩, የግልና
፪, የማሕበር(የሕግ)

፩, የግል ጾም
የግል ጾም ማለት ፦አንድ ምዕመን በራሱ መንፈሳዊ ተነሳሽነት በግሉ የሚጾመው በገዛ ፈቃዱ ከመንፈሳዊ ዝለት ከሥጋ ሕመም ለመዳን ከእግዚአብሔር ምህረት ለማግኘት ወይም በንስሐ አባት በኩል በተሰጠው ቀኖና ሥጋውን ለመቅጣት ራሱን ለመመርመር በስውር ማንም ሳያውቅ የሚጾመው ነው። በቀኖና መልክ የሚጾመው የንስሐ ጾምም ቁጥሩ ከግል ጾም ነው። የግል ጾም በስውርና ማንም ሳያውቅ ይጾማል። ለዚህም የተለያዩ መጻሕፍትን ማየት ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ነቢዩ ዳንኤል በፋርስ በነበረበት ዘመን ያሳለፋትን የሦስት ሳምንት ጾም እንዲህ ሲል ጽፎ እናነባለን፣ በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። ዳን ፲፥፪ እንዲሁም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለግል ጾም ሲናገር ስትጾሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ ለሰዎች ሊታዩ እንደ ጾመኛ ፊታቸውን ያጠወልጋሉና አንተ ግን ስትጾም ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴ ፮፥፲፮ ስለሆነም የግል ጾም አዋጅና ማስታዊቂያ የማያስፈልገው በስውር የሚጾም ጾም ማለት ነው። እንደ ልቤ የተባለው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ከኦርዮ ሚስት የወለደው ልጁ በመታመሙ ምክንያት እግዚአብሔር ልጁን ከሕመሙ እንዲፈውስለት ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ሰባት ቀን እንደ ጾመ እናነባለን እርሱም፦ ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቅስሁም። ፪ሳሙ ፲፪፥፳፪ አክሎም ይኽው ጻድቅ በጾም ተወስኖ ይኖር እንደነበር ሲናገር በመዝ ፻፰፥፳፬(109፥24 ) ወደክመኒ ብረክየ በጾም ወስሕከ ሥጋየ በኃጢአ ቅብዕ ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ። እንዲሁ ሊቀ ነቢያት ሙሴም ጽላቶቹን ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር ተራራ በወጣ ጊዜ አርባ ቀን እንደ ጾመ ነግሮናል። መጽሐፍ እንዳለ የድንጋዩን ጽላቶች፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላቶች፥ እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። ዘዳ ፱፥፱ በመሆኑም ስለ የግል ጾም አስፈላጊነትና ምንነት ሰፊ የመጻሕፍትን ሐሳቦች ማንሳት እንችላለን።

፪, የሕግ ጾም
የሕግ ጾም ማለት እንድንጾማቸው ሕግና ስርዓት ወጥቶላቸው በማሕበር፣ በአዋጅ የሚፈጸም ጾም ነው። ለዚህም ሰፊ ትውፊቶችን እናገኛለን። ለምሳሌ በባቢሎን ምርኮ የአይሁድ ካህን የነበረው ካህኑ እዝራ በስደት በደረሰባቸው ግፍ በሕብረት እንደጾሙ እና ለጥያቄያቸው መልስ እንዳገኙ ጽፎ እናነባለን።መጽሐፉ እንዲህ ይነበባል ስለዚህም ነገር ጾምን፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱም ተለመነን። ዕዝራ ፰፥፳፫ በተለይ የነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ያስለወጠ የሕብረት ጾም ነበር። የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ጾሙ እግዚአብሔርም አጠፋታለሁ ያላትን ከተማ ጾም ጸሎታቸውን ተቀብሎ ታድጓቸዋል። በመሆኑም የአዋጅ ጾም ያለና የነበረ መሆኑን መጠነ ሰፊ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል። በኦሪትም በሐዲስ ኪዳንም ነቢያት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስለ ጾም አስተምረዋል። ነቢዩ ኢዩኤል ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ ይላል። በመሆኑም የአዋጅ አጽዋማት በተለያዩ ጊዜያትና ወራት ይከናወናሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዘመኑ የሚጾሙ ሰባት የአጽዋማት ዘመናት አሉ። እነዚህም ሰባቱ አጽዋማት በመባል ይታወቃሉ። የአጽዋማቱ የየራሳቸው ሰፊ ታሪክና ምሳሌ ያላቸው ቢሆንም በዚህ እርዕስ ዝርዝር ቁጥራቸውን ብቻ እናያለን።
፩, ጾመ ነቢያት(የነቢያት ጾም) ፭, ጾመ ሐዋርያት( ሰኔ ጾም)
፪, ጾመ ገሃድ( የጥምቀት ዋዜማ የሚጾም) ፮, ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ)
፫, ጾመ ነነዌ (የነነዌ ጾም) ፯, ጾመ ፍልሰታ (ጾመ ማርያም)
፬, ዐቢይ ጾም( ሁዳዴ ጾም)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ከሰባት ዓመት የዕድሜ ገደብ ጀምሮ እነዚህን አጽዋማት እንዲጾም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስተምራሉ። ምዕመናን እነዚህን አጽዋማትን በመጾም ስርየተ ኃጢአት ያገኛሉ። የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ እንዲህ ሲል አስተምሮአል በጾም ወበጸሎት ይሠረይ ኃጢአት (በጾምና በጸሎት ኃጢአት ይሠረያል) በመሆኑም አማኞች ስርየት ያገኛሉ ይከብራሉ። ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንቀጸ ብፁዓን በሚባለው ትምህርቱ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ከዘረዘራቸው አንዱ ስለ ጽድቅ መጾም ነበር። ስለጽድቅ ብለው የሚራቡና የሚጠሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው እነርሱ ይጠግባሉና ሲል አስተምሮአል። ስለ ጽድቅ መራብ ስለጽድቅ መጠማት በቅድመ እግዚአብሔር ክብር ነውና። አንዳንድ ጊዜ ከእህል ውኃ መከልከላችን ብቻውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን ይመስለን ይሆናል። ጾም ስለታወጀ የጾም ወራት ስለሆነ ወይም ሌሎች ስለሚጾሙም አይደለም። ጾም ወደ እግዚአብሔር ከሚያደርሱ መንገዶች አንዱ ስለሆነ ነው። ጾመህ ስትበላ የተራቡ እንደሚኖሩ ማሰብ ስትለብስ የሚበርዳቸው እንዳሉ ማሰብ ጾሙን እንከን የሌለው በቅድመ እግዚአብሔር የተወደደ ያደርገዋል። በመሆኑም ጾምና ጸሎት ምጽዋት የመንፈስ መሳሪያዎች ናቸው። ታዲያ ጾማችን እንዴት እንጹም የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መጽሐፍ የጾምን መስፈርት ሲያስቀምጥ የመጀመሪያው የበደልን እስራት ፍታ ይላል። በይቅርታ፣ በትሕትና እና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት። አፋችን እስኪለውጥ ብንጾም የበደልን እስራት ካልፈታን፣ቅንነት ከጎደለው ከመንፈሳዊ ዝለት ሊያነሳን አይችልም። መጽሐፍ እንዲህ ይላል እፎ ጾምነሂ ወኢሰማይከነ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ያስነብበናል። ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ኢሳ ፶፰፥፫

በመሆኑም ጾም ጸሎታችን ምጽዋታችን በእግዚአብሔር ፊት እዲቀርብ መስፈርቱን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል።
አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን አሜን

መልአከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ኃይሌ
ልዮን ፈረንሳይ