ባሕረ ሐሳብ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፣

ንቀድም በረድኤተ እግዚአብሔር መጽሐፈ ባሕረ ሐሳብ በአብ ስም አምነን፣አብን ወላዲ ብለን፣ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሰራፂ ብለን፣ እናምናለን። ምንም ለአጥይቆ አካላት ፫ቱን በስም በአካል በግብር ፫ ብንል በባሕርይ በህልውና በፈቃድ ፩ አምላክ ብለን እናምናለን አንድም አብን ልብ፣ ወልድን ቃል፣ መንፈስ ቅዱስን እስትንፋስ፣ ብለን በማመን በረድኤተ እግዚአብሔር ባሕረ ሐሳብ እንጀምራለን። እንኳንስ መንፈዊ ሥጋዊም ቢሆን ያለ እግዚአብሔር አጋዥነት አይፈጸምምና ወኩላ ፍድፋዴ እንተ ይገብራ ብእሲ ኢትትፈጸም ዘእንበለ በረድኤተ እግዚአብሔር ወዘእንበሌየሰ ኢትክሉ ገቢረ ወኢምንትኒ እንዲል። ባሕረ ሐሳብ ማለት የተዛወረ ቃል ሲሆን ሐሳበ ባሕር ሲል ነው። ባሕር ያለው ዘመንን ነው።እስመ በመዳሉ ደለወ ዓለመ ወበመስፈርቱ ሰፈራ ለባሕር እዲል ። ሐሳብ ማለት ቁጥር ነው ሐሰበ ቆጠረ አንድም ብጹዓን እለ ትሀድገሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኩሎ ጌጋዮሙ እንዲል ። ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ አስቦም አልቀረ ፈጠረ።

ሲፈጥርም፣ ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለመውረስ ፈጠረ፣ የቀረውን ፍጥረታት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ፣ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ፣ ፈጠረ ወኩሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ንባብ፣ ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ እንዲል። እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቆጠር ፍጡር ተናግሮ ባልፈጸመው ነበር። ነገር ግን በየወገኑ ብዙውን አንድ እያሉ ቢቆጠር ከእሑድ እስከ ዓርብ ፳፪ ፍጥረታትን ፈጠረ። ፳፪ኛው አዳም ነው፣ አዳምን በነፍስ ሕያው አድርጎ፣ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ፣ ከአንዲት ዕፀ በለስ በቀር ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ ብላ ጠጣ ብሎ በገነት አኖረው። እሱም ትዕዛዙን ጠብቆ ሕጉን አክብሮ ሰባት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ምክረ ክይሲን ሰምቶ፣ አምላክነትን ሽቶ፣ ዕፀ በለስን በልቶ፣ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ፣ ከገነት ወጣ። በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በዕርደተ መቃብር ርደተ ገሀነም፣ ተፈረደበት። እሱም በፈታሒነቱ አንፃር መሐሪነቱ እንዳለ አውቆ፣ ንስሐ ገባ። ጌታም በሐምስ ዕለት፣ ወበ መንፈቃ ለ ዕለት፣ እትወለድ እም ወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ ምርህብከ ወእከውን ህፃነ በእንቲአከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ ብሎ ተስፋ ነገረው፣ እሱም ይህን ተስፋ ለልጆቹ ነገረ እነሱም እኩሌቶቹ በፀሐይ፣ እኩሌቶቹ በጨረቃ፣ እኩሌቶቹ በከዋክብት፣ እየቆጠሩ የአምላክን ልጅ ሰው መሆን ይጠባበቁ ነበር፣ ቁጥር የተጀመረው በዚህ ምክንያት ነው።

ከዚህም በኋላ የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ አምላክ፣ ቅድመ ዓለም በሕሊና ያሰበውን፣ ድህረ ዓለም በ ነቢያት ያናገረውን፣ ለመፈጸም ሰው ሆነ። ሥጋ ለበሰ። ሕገ ጠባይአዊይን ሕገ መንፈሳዊን ሲፈጽም አደገ ።ሕገ ጠባይ አበ፣ እመ ፣ ማለት ጺም፣ ጥፍር፣ ማብቀል፣ ለእናት ለዘመድ መታዘዝ፣ በየጥቂቱ ማደግ ነው። በበሕቅ ልህቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለእሙ ወለይእቲ እሞሙ እንዲል ሕገ መንፈሳዊ በ ስምንት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ፣ ለበዓል በዓመት ሶስት ጊዜ መውጣት ነው።ለያስተርኢ ተበትከ ስልሰ ጊዜያተ ምዕረ በበ ዓመት ወዘሂ አርገ ለበዓል ውእቱ እግዚአ ለኦሪት እንዲል ጌታም በ ፲፪ዓመቱ ከዘመዶቹ ተለይቶ ለማስተማር ወጥቷል በ ፴ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በ ዮርዳኖስ ተጠመቀ። ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆረንቶስ ገብቶ ፵ መዓልት፣፵ ሌሊት ጾመ። መዋዕለ ጾሙን ሲፈጽም ዲያብሎስ በሶስት አርስተ ኃጣውዕ መጣበት። በስስት፣በትዕቢት፣በአፍቅሮ ንዋይ፣ ጌታም በሶስት አርስተ ምግባራት ድል ነስቶታል። በስስት ቢመጣ በትዕግስት፣ በትቢት ቢመጣ በትህትና፣ በአፍቅሮ ንዋይ ቢመጣ በጸሊአ ንዋይ፣ ድል ነስቶታል። ምድረ እስራኤል ገብቶ ትምህርትና ታምራት ጀመረ።

የቃሉን ትምህርት የእጁን ታምራት ሰምተው ከአሥር አህጉር ከብዙ መንደር ተሰብስበው የአምስት ገበያ ያህል ሰዎች ይከተሉት ነበር።
ከነዚያም መቶ ሃያ ቤተሰብን መረጠ። መጀመርያ ሐዋርያትን መረጠ ወኀረየ እምዚአሁ ሐዋረያተ እንዲል፣ ሁለተኛም፣ ሰባ ሁለቱን አርድዕት ሰላሣ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት ናቸው። እነሱም ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ሶስት ዓመት ከሦስት ወር ትምህርት ታምራቱ አይለያቸውም። ለሌሎች ግን ምሴት ይከለክላቸዋል። ወንጌልን አስተማረ ለመድኃኒተ ዓለም በቀራንዮ ተሰቀለ። ምነው ብዙ መካን(ቦታ) አልነበረምን ?ቢሉ ትንቢቱ እና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው ትንቢቱም ወገብረ መድሃኒተ በማዕከለ ምድር ተብሎ ተነግሯልና። እራሱም ኢይደልዎ ለነቢይ መዊት በአፍአ ዘዕንበለ በኢየሩሳሌም ብሏል ። ምሳሌው አዳም በዚያ ተቀብሯልና፣ ፈጽሞ እሱን እንደካሰ ለማጠየቅ ነው። ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ በሞቱ ዓለምን አድኖ ተነሣ። በሰኑይ ዕለት ይሰርየነ ወየሐይወነ አመ ሳልስት ዕለት ሶጣ ለነፍሱ ውስተ ሦጋሁ ወአመሳልስት ዕለት ንትነሳዕ ወንቀውም ምስሌሁ እንዲል።

ከትንሣኤው በኋላም መጽሐፈ ኪዳንን ለሐዋርያት አርባ ቀን አስተማረ እንዲህ ስለሆነ እንደ ቀድሞ ሰው ሰብስቦ ጉባኤ ሰርቶ አይደለም። ለአንዱም ለሁለቱም ነው እንጂ። ዛሬ ንጉሦ ልሰወር ባለጊዜ ለአንዱም ለሁለቱም ባለሟሎቹ ሳይገለጥ እንዳይውል ለመላው ግን የተገለጸላቸው ሶስት ቀን ብቻ ነው። የትንሣኤ ፣የአግቦተ ግብር፣ የጥብርያዶስ። ወዝንቱ ሳልሱ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘአስተራዮሙ ለአርዳኢሁ ተንሲኦ እምነ ሙታን እንዲል። ከዚህ ብኋላ ትዕዛዝ አዝዟቸዋል ተስፋ ሰጥቶአቸው ዐረገ ትዕዛዙም ሑሩ ወመሐሩ ዉስተ ኩሉ አጽናፈ ዓለም ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ያለው ነው።ተስፋው፣ ጽንሑ ተስፋሁ ለአብ አንትሙሰ ንበሩ በሐገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እማርያም ያለው ነው።

በተነሣአ በ፵ ቀን በዐረገ በ ፲ ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው።ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብሌት ታደሱ፣ በአእምሮ ጎለመሱ፣ ብሌት፣ ኃጢአት ተሐድሶ፣ ልጅነትንስ በጸሎተ ሐሙስ በሕጽበተ እግር አግኝተዉታል ቢሉ ? ፍርሐት፣ ተሐድሶ፣ጥብአት እውቀት በአንድ ቋንቋ መናገር ተሐድሶ በ፸፪ት ቋንቋ መናገር ነው።
በየሩሳሌም ዓመት አስተምረዋል። ወነበሩ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ዓመተ ፍጽምተ እንዲል እነሱም ሑሩ ወመሐሩ ያላቸውን ያውቃሉና፣ ለስብከተ ወንጌል ሲፋጠኑ ይህን ሳያስተምሩት ቀርተዋል። አንድም እሱ እንደሚነሳ ያዉቃሉና፣ ስሙ ይጠራበት ብለው ትተዉታል። የቀድሞ ሰዎች ቁጥር ከዘመን ብዛት የተነሳ፣ ቁጥር ቢፋለስባቸው ነነዌን በጥር፣ አቢይ ጾምን በየካቲት፣ ሕማማትን በመጋቢት፣ እየጀመሩ በዓል ሳይዙ ከጾም ያርፉ ነበር። ትንሣኤንም ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ፣ ያውሉ ነበር። ይህ ሲያያዝ እስከ ዘመነ ድሜጥሮስ ደረሰ። እሱም ጌታ በዐረገ በ፻፹ ዓ. ም ተነስቷል።ይህ ባሕረ ሐሳብ ተገልጾለት አስተምሮታል። ከድሜጥሮስ በፊት የነበረው አቆጣጠር፣ በዓላትንና አጽዋማትን፣ የማውጣት ሂደት በቀደሙ አባቶች በነቢያት በሱባዔ እና በኢዮቤልዩ ይቆጠር ነበር ነገር ግን፣ አጽዋማትና በዓላትን በጥንተ ዕለታቸው ለማክበር አልተቻለም ነበር። የእስክንድርያ ፲፪ኛው ሊቀ ጳጳስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር ይህን ባሕረ ሐሳብ እንደገለጸለት፣ ለሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጽፎ ላከላቸው። እነሱም ሐዋርያት በዲድስቅልያ ካስተማሩት ጋር አንድ ቢሆንላቸው ተቀብለው አስተምረውታል። ይህን ባሕረ ሐሳብ ሁሉ ይማረው ዘንድ ይገባዋል ባሕረ ሐሳብ የማያውቅ ካህን ውሃ የሌለው ደረቅ ወንዝን ይመስላል። ይህም ደረቅ ወንዝ ነጋዴዎች አልፈው ሲሄዱ፣ ታላቅ ዛፍ ጫፉ ረዝሞ፣ ቅጠሉ ለምልሞ፣ ባዩት ጊዜ ውሃ ያለው መስሏቸው፣ ከጥላው አርፈን፣ ጥሬ ቆርጥመን፣ ውሃ ጠጥተን፣ እንነሳ ብለው ይሄዳሉ። ውሃ ሲያጡበት አዝነው፣ ተክዘው፣ ተሳቀው፣ ይመለሳሉ። ምዕመናንም ካህን አምሮ፣ ጠምጥሞ፣ ልብሱን አነጣጥቶ፣ መነሳንሱን ይዞ፣ ባዩት ጌዜ፣ የተማረ መስሏቸው፣ አባታችን አጽዋማትን በዓላትን አውጥቶ ይነግረናል፣ ብለው ሊጠይቁት ይሄዳሉ። ፍሬ ነገርም ሲያጡበት አዝነው ተሳቀው ይመለሳሉ። ካህን ዘኢየአምር ባሕረ ሐሳብ ይመስል ከመፈለግ ዘአልቦ ማይ ወከመ ሀገር ዘአልቦ ጥቅም እንዲል ትውልዱም ከዚህ ይናገሩታል፣ ታሪኩም እንዲህ ነው።
አርማስቆስና ደማስቆስ የሚባሉ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ ልጆቻቸውም ድሜጥሮስና ልዕልተ ወይን ይባላሉ። ድሜጥሮስ ማለት፣መጽሔት (መስተዋት) ማለት ነው። መስተዋት የረቀቀውን አጉልቶ፣ የራቀውን አቅርቦ ፣እንደሚያሳይ እሱም አጽዋማትንና በዓላትን አሰባስቦ ዘመናትን አቅርቦ በሚያሳይ መጽሔት ተመሠለ።ድሜጥሮስ በእስክንድርያ ሀገር ሃይማኖታቸው ከጸና ምግባራቸው ከቀና ቤተሰብ የተወለደ፣ ቅዱስና ንጹሕ ሰው ነበረ። የልዕልተ ወይን አባት ልጄ ልዕልተ ውይንን ከ፲፭ ዓመት በታች አታጋቧት፣ ከ ፲፭ ዓመት በላይ አታሳልፏት፣ ለአሕዛብ አትስጧት ንጽሐ ሃይማኖት ከሚፈርስ ንጽሐ ስጋ ይፍረስ ብሎ አረፈ።

በዚያን ዘመንም መናፍቃን የበዙበት ሃይማኖት የተዳከመበት ጊዜ ነበርና፣ ድሜጥሮስ ለአቅመ አዳም ሲደርስ፣ አባት እናቱ ለሱ ሚስት ትሆነው ዘንድ በሃይማኖት የምትስማማው ሴት በማጣታቸው ከሱ ጋር ያሳደጓትን የአጎቱን ልጅ «ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ) ብለው ሰርግ ደግሰው ዳሩለት። አንድም የልጀቷ አባት ሲሞት ልጄን ለአሕዛብ እንዳትድሯት ብሎ ተናዞ ስለነበር።
እሱም ወንድ እንደመሆኑ ሕግ ለማድረስ ሲጠይቃት፣ እኅትነቴን እያወቅህ እንዴት ትጠይቀኛለህ አለችው። እሱም እሽ አንቺ ካልሽ እኔም በቃልሽ እስማማለሁ ካለ በኋላ ይህንን ጉዳይ (በምሥጢር)እንያዘው ከተሠማ እኔንም አንቺንም ለሌላ ለአሕዛብ ይድሩናልና ንጽሕናችንን ጠብቀን በስውር እንኑር አላት። በነገሩ ተስማምተው እሱ መስተገብረ ምድር (ገበሬ አትክልተኛ) ሆኖ፣እሷም ደግሞ የቤት እመቤት ሆነው እሱ የውጪውን፣ እሷ የቤቱን፣ እየሠሩ ባገኙት ገቢ የተራበን እያበሉ፣ የተጠማን እያጠጡ፣ የታረዘውን እያለበሱ፣ የታመመውን እየጠየቁ፣ ለዓርባ ስምንት ዓመታት (፵፰) ሲኖሩ ከንጽሕናቸውና ከቅድስናቸው የተነሳ የሰማይ መልአክ በሌሊት እየመጣ በቀኝ ክንፉ ድሜጥሮስን በግራ ደግሞ ባለቤቱን እያለበሳቸው ያድር ነበር ። ከዕለታት በአንድ ቀን ድሜጥሮስ የፀሐይ ሀሩር በበዛበት ጊዜ፣ አትክልቱን ሊጎበኝ ሲሄድ፣ አንዲት ወይን ያለጊዜዋ አብባና አፍርታ፣ ፍሬዋም በጣም የሚያስጎመጅ ሆኖ አገኛት። ከፍሬዋም አማረኝ ብሎ ትንሽ ፍሬ በጥሶ ሳይቀምስ፣ የወይን ዘለላዋን ይዞ ወደ ቤቱ ሄደ፣ ለባለቤቱም ሰጣት። እሷም ይህን የተቀደሰ ነገር እኛ ልንመገበው አይገባንም። ብላ ከአለላ ሙዳይ ሰፍታ የወይኑን እሸት በሙዳይ ውስጥ አድርጋ፣ለሊቀ ጳጳሱ ወስደህ ሰጥተህ ጸሎትና ቡራኬ ተቀብለህ ና አለችው።

በዚያን ዘመን በእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ዐሥራ አንደኛው ዙር ሊቀ ጳጳስ ዩልያኖስ በእድሜው እጅግ ያረጀ ነበር። በዚያን ወቅት አንድ ሊቀ ጳጳስ የሥራ ዘመኑ ሲያበቃ በሱባኤና በጸሎት እግዚአሔርን በመጠየቅ ቀጥሎ የሚሾመውን ይገለጽለት ስለነበር እሱም የተገለጸለትን ከፈጣሪው ጠይቆ ለምዕመናን ማስተዋወቅ አንዱ ሥራው ስለነበረ ሕዝቡ ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመውን ሊቀ ጳጳስ አስረዳን፣ ንገረን ።እያሉ ይጠይቁት ነበርና ሊቀ ጳጳስ ዩልያኖስም እኔ እግዚአሔርን በፀሎት እጠይቃለሁ፣ እናንተም ጸልዩ የሚል መልስ ይሰጣቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆነና ለሊቀ ጳጳሱ ዩልያኖስም ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው በደረቅ በጋ ፀሐይ በበረታበት ጊዜ የወይን እሽት ይዞልህ የሚመጣ አለና እሱ ነው የሚሾመው የሚል ራዕይ ተገለጠለት።ሊቀ ጳጳሱም መጥቅ መቶ ምዕመናኑን ሰብስቦ ከኔ ብኋላ የሚሾመው ያለጊዜዋ ያፈራች ወይን ይዞ ይመጣል ይናገር በከንፈሬ ይቀመጥ በወንበሬ፣አላቸው። በዚያን ስዓት ድሜጥሮስ ከሊቀ ጳጳሱ ዩልያኖስ ቤት በር ቆሞ ሰዎች አዩት። ገብተውም ለሊቀ ጳጳሱ ነገሩት፣ እርሱም ግባ በሉት አላቸው፣ ሰዎቹም ድሜጥሮስን ወደ ሊቀጳጳሱ አስገቡት፣ እርሱም ገባና መስቀል ተሳልሞ፣ እጅ ነስቶ፣ የወይን እሽቱን በሙዳይ አቀረበለት። ሊቀ ጳጳሱም የእግዚአብሔርን ሥራ በማድነቅ ድሜጥሮስን አመስግኖና ባርኮ እንዳበቃ፣ያ ያልኳችሁ ሰው ይሄ ነው አላቸው ድሜጥሮስም ተሰናብቶ ሲወጣ፣ሊቀ ጳጳሱ ከአካባቢው የነበሩትን ምዕመናን፣ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው ሊቀ ጳጳስ እሱ ነውና፣ ተከታትላችሁ ያዙት። እምቢ ይላችኋልና በርትታችሁ ያዙት አላቸው። እነርሱም ተከታትለው በታዘዙት መሠረት ያዙት። ድሜጥሮስም ለምንድን ነው የምትይዙኝ አላቸው። አባታችን ከእኔ ቀጥሎ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው እሱ ነው ብሎናልና ጳጳስ ትሆንልናለህ አሉት። እሱ ግን በምሁሩ ወንበር እኔ መሀይሙ በጻድቁ ወንበር እኔ ኃጥኡ በድንግሉ ወንበር እኔ ባለ ሚስት (ባለ ትዳር)፣ ፣ እንዴት ሊሆንልኝ ይችላል? አላቸው። እነርሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ቤተክርስቲያናችን ሕግ አባታችን ሊቀ ጳጳስ ዩልያኖስ የፈቀዱልን አንተን ብቻ ነው ብለው አስገደዱት። በዚህ ሂደት ውስጥ ሊቀ ጳጳስ ዩልያኖስ ተዳክሞ ነበርና ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ አረፈ። ይህ መንበረ ሊቀ ጵጵስና ያለ አባት (ያለ ሊቀ ጳጳስ) መዋል ማደር የለበትም ተብሎ ይታመን ስለነበር፣ ወዲያውኑ ተሾምልን ብለው አስገደዱት። በዚያን ቀን ድሜጥሮስ ፤ የእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሥራ ሁለተኛው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ።ድሜጥሮስም አንድ ሊቀ ጳጳስ ሲሾም ሊያደርግ የሚገባውን ሕጋችሁን ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም አልተማርኩም አልከን እንጂ፣ ሕጉማ አንቀጸ ብፁዓንንና አንቀጸ አባግዕን፣ በቃሉ አንብቦ ተርጉሞ ማስረዳት ነበር አሉት። በዚህን ጊዜ ድሜጥሮስ ምንም ሞያ ሳይኖረው፣ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት አንቀፀ ብፁዓንንና አንቀፀ አባግዕን አንብቦ ተረጎመላቸው። በአግልግሎቱም በጸሎት የሚተጋ ምዕመናንን በፍቅርና በአንድነት በመልካም የሚአስተዳደር፣ ነበር ቅድስናው ይበልጥ እየሰፋ (እየበዛ) በመሔዱ በሰዎች ሰውነት ላይ በኃጢኣት የጎደፈውንና ንጹሑን ሰው የመለየት ስጦታ ተሰጠው። በዚያን ወቅት ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ሲቀርቡ፣ አንተ ለሥጋ ወደሙ አልበቃህምና ተመልሰህ ንሥሐ ግባ፣ አንቺም አልበቃሽምና ንስሐ ግቢ፣ የበቁትን ደግሞ አንተ በቅተሀልና ተቀበል፣ አንቺ በቅተሻልና ተቀበይ፣ እያለ ሊቀ ጳጳስ ነኝ ብሎ ክብሩን ጠብቆ ወንበር ላይ ሳይቀመጥ ታጥቆና አደግድጎ ያስተናግድ ነበር። በዚያን ጊዜ ምዕመናኑ ይህ ሰው አንደኛ ባለ ሚስት፣ ሁለተኛ ያልተማረ ሰው፣ ሆኖ እያለ ፣እኛ በላያችን ላይ አሠልጥነነው፣ እንዴት እኛን አንተ ውጣ፣ አንተ ግባ፣ እያለ ያዋርደናል? እያሉ ያሙት ጀመር፡ ከዚህ በኋላ መልአኩ የሕዝቡን በሐሜት መጎዳት አይቶ ክስት ክብረከ ከመ ኢይትሀጎሉ ህዝብ በእንቲአከ። አንተ የራስህን መዳን ብቻ አትሻ በአንተ ሥር ያሉ ምእመናን ሁሉ አንተን በማማት እየተጎዱ ነውና፣ የአንተን ምሥጢራዊ ሥራ ግለጽላቸው አለው። እሱም ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንብኝ እንጂ እሽ፣ በጎ ፣ብሎ ጊዜ ሳይወስድ አስቦ እያንዳንዱ ምዕመናን የተቻለቸውን ያህል እንጨት እንዲያመጡ አዘዘ። ሁለም ምዕመናን እንዳዘዛቸው፣ እንጨቱን በዕለተ ሰንበት ለቅዳሴ ሲመጡ ይዘው መጡ። ሊቀ ጳጳስ ድሜጥሮስ ምዕመናኑ ይዘዉት የመጡትን እንጨት አንድ ቦታላይ ደመረውና እሳት አያይዞት ቅዳሴ ገባ። ፍላጎቱም እንጨቱን አቀጣጥሎ፣ በነዲዱ በመመላለስ ክብሩን ለመግለጽ ነበርና። ምዕመናኑ አሁንም አንተ ግባ አንተ ውጣ እያለ ሲያስቸግረን ቆይቶ ሊያቃጥለን ነው እንዴ? እያሉ ያጉረመርሙ ጀመር። እርሱ ግን ቀድሶ እንደወጣና ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ ጽናውን ይዞ ኦአምላክ ዘለዓለም ቀዳሚ ወደኃሪ ዘአልብከ ጥንት ወኢተፍጻሜት…….እያለ ገባ ባለቤቱንም ጠርቶ በሚቃጠለው ደመራ ፊት ለፊት ምዕመናኑን እጅ በመንሳት ሁለቱም ወደሚቃጠለው ደመራ ውስጥ ገቡ። ስፍሂ አጽፈኪ ልዕለተ ወይን (ልብስሽን ዘርጊ ብሎ ፍህሙን በእጅ እያፈሰ በልብሷ ያስታቅፋት ጀመር።

እሳቱ ግን ልብሳቸውንም ሆነ ሰውነታቸውን ምንም ሳይነካቸውና ጉዳት ሳያደርስባቸው በሰላም ይመላለሱ ነበር። ምዕመናንም ይህንን ባዩ ጊዜ እያደነቁ በሁኔታው ደነገጡ። ከዚህ በኋላ መልአኩ በህልም እንደገለጸለት ለ፵፰ ዓመታት አብረው ሲኖሩ በግብር ሳይተዋወቁ በንጽሕና መኖራቸውን ገልጾላቸዋል። ምዕመናኑም ኦአባ ስረይ ለነ አባታችን ይቅር በለን በድለናል ብለው ከእግሩ ሥር ወደቁ። እንደገናም አባታችን ሆይ እኛስ ባለማወቃችን ነው አንተ ግን ለምን አስቀድመህ ይህንን ክብር አልገለጽክልንም? ብለው ጠየቁት። እርሱም እኔ ያልገለፅኩላችሁ ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል ብዬ ነው። አሁን ግን የእናንተን በሐሜት መጎዳት አይቶ መልአኩ ግለጽላቸው ብሎ ስላዛዘኝ ይህንን ነገር ልገልጸላችሁ ቻልኩ ብሎ አስረዳቸው። ይህንን ቃል በማስረዳት ብቻም አልተወም። ናዝዞ ከኃጢአታቸው ፈታቸው እንጂ እንዲህ ብሎ፤ ይፍታሕ ይሕድግ ወያሰተስርይ እግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሰራየ ኃጢኣት ወደምሳሴ አበሳ ይስረይ ለክሙ
ኃጢአተክሙ እምንዕስክሙ እስከ ይእዜ ብሎ አሥራ ሁለት ጊዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስና በእንተ እግዝእትነ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ እንዲሉ አዝዟቸዋል።ኑዛዜንም የጀመረው እርሱ ነው።

ድሜጥሮስ በእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ የእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሥራ ሁለተኛው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ እንደተሾመ፤ ከዚያ በፊት በዘመነ ሐዋርያት ያልተፈጸመውን አጽዋማትና በዓላትን ጥንተ ዕለታቸውን ሳይለቁ በየጥንተ ዕለታቸው እንዲከበሩ ለማድረግ ይመኝ ነበር። እግዚአብሔር አምላክም ለፍጡሩ ርኀሩኀ ነውና መልአኩን ልኮ ነገር ሁሉ በምኞት አይፈጸምምና ሱባኤ ገብተህ እየው ብሎታል። ድሜጥሮስም ቀን ቀን ከተሰጠው የሀላፊነት ሥራ በላይ ሕሙማንን ሲጠይቅ፣ የተቸገሩትን ሲረዳ፣ የተጣላ ሲያስታርቅ፣ በአጠቃላይ በበጎ ሥራ ላይ ተጠምዶ ይውል ስለነበረ በየቀኑ ፯ ሱባኤ ያደርስ ነበር፡፡ ሌሊት ግን የሚሰራው ብዙ ስራ ስለሌለው ዘወትር ፳፫ ጊዜ ሱባኤ ያደርስ ነበር፣ መልአኩም ፯ቱን ሱባኤ በ፯ አብዝተህ በ፴ ገድፈህ ትርፉን ያዝ አለው። የ፯ቱ ሱባኤ ድምር ፵፱ ይሆናል በ፴ሲገደፍ ትርፉ፲፱ ይሆናል። ይህን መጥቅዕ በለው ብሎታል። ፲፱ ጥንተ መጥቅዕ ነው። መጥቅዕ ማለት ደወል ማለት ነው። ደወል ሲደወል(ሲመታ) የራቀው ይቀርባል ፤ የተኛው ይነሣል ፤ የተበታተነው ይሰበሰባል። ይህም ቀመር መጥቅዕ የተባለው የተበተኑትን አጽዋማትና በዓላትን በማሰባሰብ የራቀውን ዘመን አቅርቦ ስለሚያሳይ ነው። የሌሊቱ ፳፫ በ፯ ሲባዛ ፻፷፩ ይሁናል ይህም በ፴ አምስት ጊዜ ሲገደፍ ፲፩ ይሁናል፣ ፲፩ ጥንተ አበቅቴ ነው፣አበቅቴ ማለት ተረፈ መዓልት (ሌሊት) ማለት ነው።በዓላትና አጽዋማትን ለማውጣት የሚያገለግሉን መስፈሪያ ፯ አእዋዳት አሉ። እነሱም አውደ ዕለት፣ አውደ ወርኅ፣አውደ ዓመት፣አውደ አበቅቴ፣ አውደ ፀሐይ፣ አውደ ማህተም፣አውደ ቀመር ናቸው። አውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባት ዕለታት ናቸው። እነዚህም አውራኅን ለማስገኘት በሰባት በሰባት ሲመላለሱ ይኖራሉ ። አውደ ወርኅ በጨረቃ አንድ ጊዜ ፳፱፣ አንድ ጊዜ ፴ ሲሆን በፀሐይ ግን ዘወትር ፴ ነው። ይህም አውደ ዓመትን ለማስገኘት ሲመላለስ ይኖራል አውደ ዓመት በ ፀሐይ ፫፻፷፭ ዕለት ከ፲፭ ኬክሮስ፣ ከ፮ካልዕት ፣በጨረቃ ፫፻፶፬ ዕለት፣ ከ፳፪ ኬክሮስ ፣ከ፩ካልዕት ነው።ዕለታትን አእዋድ አላቸው አውራኅን የሚያስገኙ ስለሆነ፣ አውራኅን አእዋድ አላቸው ዓመታትን የሚያስገኙ ስለሆኑ በከመ ይትወለዱ አውራኅ እምዕለታት ወዓመታት እም አውራኅ ከማሁ ይትወለዱ አእምሮታት እምግባራት ወእመከራት ዘቦቱ ያነጽህ አውደ እክሉ እንዲል።
ከሰባቱ ፫ቱ በዕለት፣ ፬ቱ በዓመት፣ ይቆጠራሉ። በዕለት በዕለት የሚቆጠሩት ፫ቱ አውደ ዕለት፣አውደ ወርኅ፣አውደ ዓመት ናቸው።በዓመት የሚቆጠሩት አራቱ ግን አውደ አበቅቴ፣ አውደ ፀሐይ፣ አውደ ማህተም ፣አውደ ቀመር ናቸው። አውደ አበቅቴ ፲፱ ዓመት ነው። በዚህም ፀሐይና ጨረቃ መንገዳቸውን እየፈጸሙ በተፈጠሩበት ኆኅት ተራክቦ ያደርጋሉ። ነቢየ ኦሪት ሙሴ፣ መምህራነ ወንጌል ሐዋርያት፣ ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ፣ ከ፳ው አንድ፣ ከ፵ው ሁለት፣ ከ፷ው ሦስት፣ ከ፹ው አራት፣ከ፻ው አምስት እየነሳችሁ ቁጠሩ ማለታቸው ስለዚህ ነው። አውደ ፀሐይ ፳፰ ዓመት ነው። በዚህ ዕለት ወንጌላውያን ይገናኛሉ። ዕለቱ ረቡዕ ነው። ወንጌላዊው ማቴዎስ ዕለቱ ፀሐይ አለው። ወበትዛዝከ ይቀውም ዕለት እንዲል ወንጌላውያኑን ፀሐይ አለው አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም እንዲል።
አውደ ማኅተም ፸፮ ዓመት ነው። በዚህ ዕለት አበቀቴ ወንጌላዊው ዮሐንስ ማኀተም አለው አበቀቴው ለአበቅቴ፣ ወንጌላዊው ለወንጌላውያን፣ ፍጻሜ ስለሆነ።
አውደ ቀመር ፭፻፴፪ ዓመት ነው። በዚህ ዕለት አበቀቴ ወንጌላዊ ይገናኛሉ ሠሉስ ነው። አበቅቴው ፲፰ ነው ወንጌላዊው ማቴዎስ ፣ ቀመርን ለሦስት በሰጡ ጊዜ አውደ ቀመር አቢይ ቀመር፣አውደ ማህተም ማዕከላዊ ቀመር፣ አውደ አበቅቴ ንዕስ ቀመር ይባላሉ።

አሁን የ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረትን በዓላትና አጽዋማትን እናወጣለን። የተሾመውን ወንጌል ለማግኘት ፣በቀላሉ ዓመተ ዓለምን ለ፬ ወንጌላዊያን በማካፈል ፩ ሲቀር ማቴዎስ ፣፪ ሲቀር ማርቆስ፣ ፫ሲቀር ሉቃስ፣ እኩል ደርሶ ቀሪ ከሌለ ግን ዘመኑ ዮሐንስ ይሆኖል።ዘንድሮ ለምሳሌ ፶፻፭፻ +፳፻፲፭ = ፸፻፭፻፲፭ ÷ ፬ በባሕረ ሐሳብ ሕግ መሰረት በየቤቱ በማካፍል፣እኩል ፲፻፰፯፰ ይደርሳል ቀሪ ፫ ነው ስለዚህ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ ይሆናል። ድርሻው ፲፻፰፯፰ ደግሞ መጠነ ራብይት ይባላል።
ዕለቱን ወይም መባቻውን ለማወቅ፣ ከላይ ባገኘነው መሰረት ወንጌሉ ወይም ዘመኑ ሉቃስ ነው። የሚብትበት ቀን ወይም መባቻ ማለት መስከረም አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ የሚውልበት ማለት ነው። ከዚህ ቀጥሎ ያለው በየዓመቱ ተለዋዋጭ ስለሆነ ለአንባቢዎች ያመች ዘንድ የዓለም አቀፍ ቁጥር መጠቀም አስፈልጓል።
መባቻ = ዓመተ ዓለም + መጠነ ራብይት ÷ 7
= 7515 + 1878 ÷ 7
= 9393 ÷ 7 = 1341 ደርሶ ቀሪ 6
ከዚህ ላይ መረዳት ያለብን አለ፣ እሱም እኩል ተካፍሎ የሚተርፍ ቁጥር ሊኖር ይችላል፣ ምንም ቀሪ ላይኖር ይችላል። ስለዚህ እኩል ተካፍሎ ምንም ቀሪ ከሌለ፣ መባቻ ሰኞ ቀን ይሆናል።
 ቀሪው 1 ከሆነ ማክሰኞ
 ቀሪው 2 ከሆነ ረቡዕ
 ቀሪው 3 ከሆነ ሐሙስ
 ቀሪው 4 ከሆነ ዓርብ
 ቀሪው 5 ከሆነ ቅዳሜ
 ቀሪው 6 ከሆነ እሁድ ይሆናል
ነገር ግን ዘንድሮ በ 2015 ዓ.ም ቀሪ 6 ስለ ሆነ መባቻ እሑድ ቀን ይሆናል።
የዓመቱን በዓላትና አፅዋማት ለማውጣት አመተ ፍዳ ሲደመር ዓመተ ምህረት = ዓመተ ዓለም ÷ ለአቢይ ቀመር (532) ትርፉን ለማዕከላዊ ቀመር (76) አሁንም ትርፉን ለንዑስ ቀመር (19) ቀሪውን ወንበር። ለምሳሌ 5500 + 2015 = 7515 በየቤቱ ማካፈል፣ 7000 ÷ 532 = 13 ደርሶ ቀሪ 84
515 + 84 = 599 ለማዕከላዊ ቀመር 76 ማለትም 599 ÷ 76 = 7 ደርሶ ቀሪ 67 ይሆናል።
67ን ለንዑስ ቀመር( 19) 67 ÷ 19 = 3 ደርሶ ቀሪ 10 ይሆናል።
በሕጉ መሰረት ዘመኑ ስለተጀመረ ተቆጠረ፣ ስላልተጨረሰ ተአተተ፣ አንዱን ለዘመን እንሰጥና 9 ወንበር ይሆናል። ጥንተ መጥቅዕንና ጥንተ አበቅቴን በወንበሩ በ 9 አብዝተን በ30 ገድፈን የአዲሱን ዘመን ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ጥንተ አበቅቴ 11 ነው። 11 ×9 = 99 ነው። ዘጠናዘጠኝን በሠላሳ 3 ጊዜ ገድፈን 9 እናገኛለን። ( 30 × 3 = 90 ይሆናል። 99- 90= 9) የሁልትሺ አስራ አምስት አበቅቴ 9 ሆነ
ጥንተ መጥቅዕ 19×9 = 171 በሠላሳ አምስት ጊዜ ገድፈን 21 እናገኛለን።
(30×5 = 150 ይሆናል። 171 – 150 = 21) 21 መጥቅዕ
የ 2015 ዓ.ም አበቅቴ 9፣መጥቅዕ 21፣ ይሆናል። መጥቅና አበቅቴ አንዱ ሊበዛ ሌላው ሊያንን ይችላል ነገር ግን የሁልርቱ ድምር ከሰላሳ አይበልጥም ከሰላሳም አያንስም፣ መጥቅዕ ወአበቅቴ ክሌሆሙ ኢየአርጉ እምሠላሳ ወኢይወርዱ እምሣላሳ ወትረ ይከውኑ ሰላሳ እንዲል
አበቅቴ ከዕለታትና ከእጸጽ አውራህ ጋር እየተቆጠረ ሌሊትን ለማስገኘት ይረዳል።
መጥቅ ከዕለታት ተውሳክ ጋር እየተቆጠረ መባጃ ሐመርን ያስገኛል።
የዕለታት ተውሳክ ከቅዳሜ ይጀምራል


መጥቅዕ ቢበዛ በመስከረም ንዛ መጥቅዕ ቢያንስ በጥቅምት ዳስ መጥቅዕ 14ን አይነካም ከ14 በላይ የሆነ እንደሆነ በመስከረም ይወድቃል መጥቅዕ ከ14 በታች የሆነ እንደሆን በጥቅምት ይወድቃል ። የ2015 መጥቅዕ ከላይ እንዳየነው 21 ስለሆነ በመስከረም ይወድቃል። የመስከረም መባቻ እሑድ ነው። እሑድ ለእሑድ ስምንት እሑድ ለእሑድ አስራ አምስት ሰኞ 16 ማክሰኞ 17 ረቡዕ 18 ሐሙስ 19 ዓርብ 20 ቅዳሜ 21 በዓለ መጥቅ ቅዳሜ ምስከረም 21 ይውላል የ ቅዳሜ ተውሳክ 8 + መጥቅ 21=29 ዓ.ም መባጃ ሐመር 29 ይሆናል። በዓለ መጥቅዕ በመሰከረም ከዋለ ነነዌ በጥር ይውላል ።በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ከዋለ ነነዌ በየካቲት ይውላል። የመስከረም ሳኒታ ጥር መስከረም መባቻ እሑድ ስለሆነ ጥር መባቻ ሰኞ ይብታል። ሰኞ ለሰኞ አራት ጊዜ 29 ይሆናል።
ጾመ ነነዌ ጥር 29 ቀን ሰኞ ዋለ ማለት ነው።
 የአቢይ ፃም ተውሳክ 14፣ መባጃ ሐመር 29+14 = 43 ሰላሳውን ገድፎ 13፣ የካቲት 13 አቢይ ጾም ይገባል።
 የደብረ ዘይት ተውሳክ 11፣ መባጃ ሐ 29+11= 40 ሰላሳውን ገድፎ 10፣ መጋቢት 10 እሑድ ደብረ ዘይት ይውላል።
 የሆሣዕና ተውሳክ 2፣ መ. ሐ 29 +2=31 ሰላሳዉን ገድፎ 1፣ ሚያዝያ 1 እሁድ ሆሳዕና ይውላል።
 የስቅለት ተውሳክ 7፣ መ ሐ 29 +7= 36 ሰላሳዉን ገድፎ 6፣ ሚያዝያ 6 አርብ ስቅለትይውላል።
 የትንሳኤ ተውሳክ 9፣ መ ሐ 29+9= 38 ሰላሳዉን ገድፎ 8፣ ሚያዝያ 8 በዓለ ትንሣኤ, ይውላል።
 የርክበ ካህናት ተውሳክ 3፣ መ.ሐ29 +3= 32 ሰላሳዉንገድፎ 2፣ ግንቦት 2 ርክበ ካህናት ይውላል።
 የዕርገት ተውሳክ 18፣ መ. ሐ 29 +18= 47 ይሆናል።ሰላሳዉን ገድፎ 17፣ ግንቦት 17 ሐሙስ በዓለ ዕርገት ይውላል።
 የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28 መ.ሐ 29+28=57 ይሆናል።ሰላሳዉን ገድፎ ቀሪ 27፣ ስለዚህ ግንቦት 27 እሑድ በዓለ ጰራቅሊጦስ ይውላል።
 የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29 መ.ሐ 29+29= 58 ይሆናል። ሠላሳውን ገድፎ ቀሪ 28፣ ስለዚህ ግንቦት 28 ሰኞ ፆመ ሐዋርያት ይሆናል።
 የጾመ ድህነት(ዓርብ ረቡዕ) ተውሳክ 1 መ.ሐ 29+1= 30 ጾመ ድህነት (ዓርብ ረቡዕ )ሰኔ 30 ይውላል።

አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን አሜን።
መ/ሰ/ቀሲስ ሰሎሞን ኃይሌ ልዮን ፈረንሳይ