በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በመላው ዓለም ለምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እንኳን ለበዓለ ደብረ ቁስቋም/በዓለ ሚጠተ እግዝእትነ ማርያም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን።
ለዚህ በዓል መከበር መሠረቱ የእመቤታችን ድንግል ማርያም እና የሕፃን ልጅዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሰደድ ስለሆነ የመሰደዳቸውን መሠረታዊ ሐሳብ ማየት እና ማውሳት የግድ ነው።ስደታቸውም ትንቢቱ ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ወደ ምድረ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ነበር ትንቢት “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ምድረ ግብጽ ይመጣል የግብጽ ጣዖታትም በፊቱ ይርዳሉ የግብጽም ልብ በውስጧ ይቀልጣል„ኢሳይያስ 19፥1 ከግብጽ አምልኮተ ጣዖታትን ለማጥፋት፣የግብጽና የኢትዮጵያ ገዳማትን ለመባረክ፣ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለማጠየቅ፣ስደትን በፈቃዱ የመረጠ ሰው ነውና ሥጋን በመልበሱ ተሰደደ፣ተንገላታ፣ተራበ፣ተጠማ፣ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት፣ሰይጣንን ከሰዎች ልቡና አስወጥቶ ለማሳደድ፣“ጉየተ ሕፃን አጉየዮ ለዲያብሎስ/የሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ መሰደድ ዲያብሎስን ከሰዎች ልቡና አስወትቶ አሳደደው„እንዲል
የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ።በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ዓለምን በመሃል እጁ የያዘ አምላክ በዚች ምድር እንግዳና ስደተኛ በመሆን በኪደተ እግሩ ዓለምን ቀድሷታል።
ዓለምን የፈጠረና በመሃል እጁ የያዘ ክርስቶስ ኢየሱስን ያልተቀበለች ዓለም እኛን ክርስቶሳውያንንም እንደ ማትቀበለን አውቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ከግብጽ በሥጋ ወደ ተወለደባት ሀገሩ ገሊላ እንዲሁም በዕርገተ ሥጋ ወደ ቀደመ ክብሩ እንደተመለሰ ሁሉ እኛም ወደ ሀገራችን ገነትና መንግሥተ ሰማያት እስክንመለስ ድረስ በእንግድነት እና በስደትት አድሮ ተጓዥ በሆንባት ዓለም ማንኛውንም የዓለም ፈተና ሁሉ በመታገሥ በሃይማኖት ጸንተን በምግባር ቀንተን በፈሪሃ እግዚአብሔር እና በሥርዓት እንድንኖር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል አስተምሮናል።“እንዘ ትፈርሁ በኩሉ መዋዕለ ሕይወትክሙ ወበዘ አመንክሙ ሑሩ ባቲ/በእንግድነታችሁ ዘመን እግዚአብሔርን በመፍራት ኑሩ„1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፥17 ይህንን ቅዱስ ቃል የተናገረው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሆን ቃሉም የተነገረው የሰው ልጅ ከፍጥረታት ይልቅ ክቡር በመሆኑ በከበረ በክርስቶስ ደም የተገዛ እንጅ በሚጠፋና በሚዝግ ብርና ወርቅ እንዳልሁነ አውቆ እራሱን ከሥጋና ከነፍስ ጥፋት እንዲጠብቅ ለማስገንዘብ የተነገረ ነው።የእንግድነት ዘመን የተባለውም በዚህ ዓለም የምንኖርበት ውሱን ዕድሜአችን ነው እንግዳ አድሮ ተጓዥ እንጅ ኗሪ እንዳልሆነ ሁሉ ለእኛም ለክርስቶሳውያን ይህ ዓለም በጎ ሥራ ሠርትርን የጉዞ ስንቃችንን የምንይዝበት እንጂ መኖሪያችን እንዳልሆነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይመሰክራል።“እስመ ፈላሲ አነ ውስተ ምድር ወነግድ ከመ ኩሉ አበውየ ሥኅተኒ ከመ አዕርፍ/እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና እንደ አባቶቼም ሁሉ እንግዳ ነኝና ከመከራ ሥጋ አርፍ ዘንድ እረፍትን ስጠኝ„መዝ 38፥11 ይህ ሃላፊና ከንቱ ዓለም ለክርስቶሳውያን መከራና ስደት የሆነበትም ምክንያት ሀገራችን ስላልሆነ ነው የእኛም ሀገራችን ገነት መንግሥተ ሰማያት እንጅ ይህ ዓለም እንዳልሆነ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት አስተምሮናል።“እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው ከዚያም እርሱን መድኃኒታችን ኢየስይስ ክርስቶስን እንጥባበቃለን„ፊል 3፥20
ከሀገሩ የተሰደደ ሰው ሁሉ እረፍትና ክብር የለውም አዳም አባታችን ከሀገሩ ገነት ወጥቶ ከተሰደደ ጀምሮ ወደ ሀገሩ ገነት እስኪመለስ ድረስ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት በዚህ ምድረ ፋይድ በተባለው የስደት ዓለም በሐሳርና በድካም እንዲሁም በቀኖና ምድራዊ ሕይወቱን እንዳሳለፈ እናውቃለን የሰውም እርፍቱና ክብሩ በሀገሩ እንደሆነ ሁሉ አዳም አባታችንና የልጅ ልጆቹም ወደ ሀገራቸው ገነት ከገቡ በኋላ ክብርና ደስታን ተጎናጽፈዋል“ከእንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም„ኤፌ 2፥19
እንግዲህ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወቱ እንዲህ መሆኑን ከተረዳ ዘንድ በማያልፈውና ለዘለዓለማዊውና ሰማያዊው ዓለም ለክብርና ለምስጋ መፈጠራችንን ሳንዘነጋ በማጣት ጊዜ ሳናማርር በማግኜትም ጊዜ ሳንኩራራ ስንመጣ ይዘነው የመጣን እንደሌለን ሁሉ ስንሄድም የምንወስደው አንዳች ነገር አልመኖሩን አውቀን እንደ ጻድቁ ኢዮብ እግዚአብሔርን እንዲህ ልናመሰግን ይገባናል።“ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ ራቁቴንም ወደምድር እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን„ኢዮ 1፥21 በተለይ የኛ ዘመን ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ የፈጠነ መሆኑን በመረዳት በተፈቀደችልን ምድራዊ የኩንትራት ጊዜ እንደ ባለ አእምሮ በማሰብ ሰውና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራ እየሠራን ጥሪያችንን በተስፋ ልንጠባበቅ ይገባናል“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ„ 1ኛ ጴጥ 4፥7 ይቆየን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ማርያም ወለመስቀሉ ክቡር አሜን
አዘጋጅ መ/ሐዲስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ወርቁ ጣልያን ኡድኒ
የጽሑፍ አስተያየቶች