በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ትምህርተ ሃይማኖት /ዶግማ እና ቀኖና
በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ወይም አባት ብለን፣ በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ወይም ልጅ ብለን፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብንል በአምላክነት፣ በመለኮት፣ በባሕርይ በህልውና በፈቃድ፣ በምክር፣ በመፍጠር በእግዚአብሔርነት አንድ አምላክ ብለን አምነን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ነገረ እግዚአብሔርን እና ቀኖና አበውን መማርና ማስተማር እንጀምራለን።
መግቢያ
ትምህርተ ሃይማኖት ረቂቅ፣ ጥልቅና ምጡቅ እንደ መሆኑ ከሌላው ምርምርና ጥናት በበለጠ ትኩረት ይሻል፤ የተሰበሰበ ሕሊና እና ክት አእምሮ እንዲሁም ዝግጁነትን ይጠይቃል። ትምህርተ ሃይማኖት ስንል የቀናች፣ የጎላችና የታወቀች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማትን አስተምህሮ ይመለከታል፡፡
እምነት መሠረት ናት ሌሎቹ ሕንፃ እና ግንብ ናቸው በማለት ቅድስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚያስገነዝበን እንደ ሕንፃና ግንብ ከሚቆጠሩት ከምግባርና ከትሩፋት ሁሉ በፊት የሃይማኖትን ቀዳሚነትና መሠረትነት ነው፡፡ መሠረት ሕንፃውን ሁሉ እንደሚሸከም እምነትም ምግባርን ሁሉ ትይዛለች፡፡ ሕንፃ ያለ መሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሐይማኖት አይኖርም፡ስለሆነም ከሁሉ በፊት የሃይማኖትን ትርጉም በማስቀደም እንጀምራለን፡፡
ሃይማኖትም ‹‹ሀይመነ›› አመነ ታመነ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ፡፡ ማመን፣ መታመን፣ እምነት፣ ጽኑዕ ተስፋ፣ የአምልኮት ባህል፣ በልብ በረቂቅ ሀሳብ የሚሳል ማለት ነው። ሃይማኖት እግዚአብሔር አለ ብሎ ማመን ሲሆን «እምነት» ድግሞ ያደርግልኛል፣ ይፈጽምልኛል፣ ያከናውንልኛል ማለት ነው።
ወይም «ሃይማኖት» በጥቅሉ ወይም በሩቅ እግዚአብሔር አለ ብሎ ማመን ሲሆን «እምነት» ደገሞ በጸሎት በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር መቅረብንና የማይቋረጥ ግንኙነት መፍጠርን ያመለክታል።
ሃይማኖት የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሥራ ሁሉ መጀመሪያ እና የሥራ ሁሉ መፈፀሚያ በመሆኑ ለሰው ለጅ ከሁሉ በፊት ሃይማኖት ያስፈልገዋል። የሚከተሉት አናቀጽ ይህንን እውነት ያስረግጣሉ።
❖ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላ ውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው (ያዕ 1፥7)።
❖ መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። (መዝ 37፥5)
❖ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። (ማር 9፥23)
የሰው ልጅ ፈጣሪውን እንደ እህል ውሃ ይራባል ያለ እህልና ውሃ እንደማይኖር ያለ እግዚአብሔርም መኖር አይችልም። እውነተኛውን አምላክ ማምለክ አለማምለክ ሌላ ነገር ሁኖ የሰው ልጅ ግን ከአለበት አምላክን የመራብና የመጠማት ችግር ለመዳን ሲል ለገዛ እጁ ሥራ ሁሉ ሳይቀር ሲሰግድና ሲሠዋ እናያለን።
የቻርለስ ዳርዊን፣ የማርክስ፣ የሌኒን፣ የማኒ፣ በአጠቃላይ የደቀ መዛሙርቶቻቸው የየኮምኒስቶች አምላክ የለሽ ፖለቲካ ያላራመዳቸው እውነቱ ይህ ስለሆነ ነው።
የእግዚአብሔር መኖር
የእግዚአብሔርን መኖር መረጋገጥ ለሚፈልግ ብዙ አስተማሪዎች አሉለት ። መምህራን፣ሥነ ፍጥረት፣ ሕሊና ወይም የራሱ የተፈጥሮ ዝንባሌ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩታል።
❖ የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ» (ሮሜ 1÷21)።
❖ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። (ዕብ 11÷3)።
❖ ዘለዓለም የሚኖር የእግዚአብሔር ሕጉን ጠይቃችሁ ዕወቁ (ኤር 6÷16)።
❖ እኛ ግን ወንጌልን የሚያስተምሩ መምህራንን አብነት እናደርጋለን (ቅ.ማርያም)።
❖ ያስተማረኝ ሳይኖር በምን አውቀዋለሁ አለው (ሐዋ.ሥ. 8÷31)።
❖ ወንጌልን ያስተማሯችሁ መምህሮቻችሁንም እርዱ (ዕብ 13÷7)።
እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ከርቀቱ/መንፈስነቱ ፣ ከኃይሉ ብዛት፣ ከነደ እሳትነቱ የተነሣ ልናየው የማንችለው እና በአምላክነቱ ታይቶ የማያውቅ እግዚአብሔር መኖሩ በሥነ ፍጥረት ይታወቃል ይላል። ባለመኖር አይታይ የነበረው ዓለም በእግዚአብሔር ሥልጣን ካለመኖር ወደመኖር መጥቶ እንደታየ እና ፈጠሪ አስገኚ ሠሪ እንዳለው እናውቃለን በማለት የቻርለስ ዳርዊንን፣ የማርክስን፣ የማኒን፣ የኮምኒስቶችን ወሬ ከንቱ አድርጎታል።
ከላይ በጥቅሶቹ እንዳየነው ስለ እግዛብሔር መኖር ከራሳችን ተፍጥሮና አምላክን የመፈልግ ዝንባሌ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት፣ከሥነ ፍጥረት /የፍጥረቱ ምስክርነት እና ከመምህራን ማረጋገጥ እንደሚቻል እንረዳለን። ቀጥሎ የእግዚአብሔርን ባሕርያት የሚሻገሩና የማይሻገሩ ብለን በሁለት መንገድ ባጭር ባጭሩ እናያለን።
የማይሻገሩ የእግዚአብሔር ባሕርያት
ሀ/ ዘለዓለማዊ ነው።
❖ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ (ኢሳ 44፥6)። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ (ራእ 22፥13)። ከእርሱ በቀር ዘላለማዊ የለም።
ለ/ ሁሉን አዋቂ ነው።
❖ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። (ዮሐ 21፥17)። ከእርሱ በቀር ሁሉን አዋቂ የለም።
ሐ/ በሁሉ የመላ ምሉዕ ነው።
❖ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።(ኤፌ 4፥6)።
❖ ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች (መዝ 139፥7)። ከእርሱ በቀር በሁሉ የመላ የለም።
መ/ ሁሉን ቻይ ነው።
❖ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም (ሉቃ.1፥37)። እንዳለ ቅ/ገብርኤል
❖ አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ (ሁሉን ቻይ) ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን አለው (ዘፍ 17፥1)። ሁሉን ቻይ ከእርሱ በቀር የለም።
ሠ/ አይለወጥም።
❖ አንተሰ አንተ ክመ ወዓመቲከኒ ዘኢየኀልቅ= ትርጉምም አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። (መዝ 102፥27) ማለት ነው። ሁሉ ያረጃል የለወጣል እርሱ ከዘላለም ያው ነው።
የእግዚአብሔር ተሻጋሪ ባሕርያት
የእግዚአብሔር ተሻጋሪ ባሕርያት ማለት በተወሰነ ደረጃ ወደፍጡራን ወደ ሰውና መልእክት የሚሻገሩ ወይም ለእነዚህ ፍጡራን የሚሳጣቸው ማለት ነው።
ሀ/ ቅዱስ ነው ።
❖ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ (ኢሳ 44፥6)። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ (ራእ 22፥13)። ከእርሱ በቀር ዘላለማዊ የለም።
ለ/ ፍቅር ነው።
❖ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና (ዮሐ 3፥16-17)። እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። (1ኛዮሐ 4፥16)።
ሐ/ ጥበበኛ ነው።
❖ ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም። (መዝ 147፥5)።
❖ በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት (ዘፀ.31፥3)
መ/ ቸር፣ መሐሪ፣ጻድቅ ይቅር ባይ ነው፡፡
❖ እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ ጻድቅ ነው፡፡ (መዝ 102፥8)።
❖ እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ። (ኢሳ.63፥7)።
ሃይማኖት /በእግዚአብሔር ማመን/ ለምን ይጠቅማል?
ንጹሕ አየር የማያስፈልገው ሰው ሊኖር ይችል ይሆን? የደማዊት ነፍስ ሕይወቷ አየር ከሌለ የነፍሰ ባሕርይ ከምን ጋር ተዋሕዶ ሰው በሕይወት ሊኖር ይችላል? የነፍስ ሕይወት ተአምኖ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነፍስ ከቃለ እግዚአብሔር ከተአምኖ እግዚአብሔር ተለይታ ምውት ሆና ከቆየች በኋላ እግዚአብሔርን በሰማች ጊዜ ተአምኖ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርጋ ሕያው መሆን ትችላለች፡
የማይፈራ ፍጡርስ ሊኖር ይችላልን? ሰው ለምን ይፈራል? በፍርሃት ጊዜ የሚፈልገው ምንድነው? ሊፈራ የማይችል አካል ሊኖር ይችላል? ካለ ማን ነው? ከሌለስ ለምን? እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል ስለሆነ ሁሉም ፍጥረት ደግሞ ከእርሱ በእርሱ እና ለእርሱ ስለተከናወነ ማንንም ሊፈራ አይችልም፡፡ ፍጥረት ሁሉ ግን የሚሆነውን ካለማወቅ ከእርሱም የሚበልጥ አካል ስላለበት፤ ሁል ጊዜ እርዳታ ስለሚያስፈልገው ሊፈራ ይችላል፡፡ ከስሕተት በኋላ ከመጡ የሐጢአት ውጤት ከሆኑት ከከበቡት በርካታ ችግሮች የተነሣ ርዳታ በመፈለግ ብቻ ሳይሆን ሰው በተፈጥሮው አምላክን የመፈለግ የሃይማኖተኛነት ባሕርይ አለው። የሥነ መለኮት ሊቃውንት «ሃይማኖት» በሰው ላይ ከጊዜ በኋላ የተጫነ በዕድ ነገር አይደለም ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ለዚህ ነው።
ያለ ሃይማኖት እግዚአብሔርን ማየትና ማወቅ አይቻልም። ካላወቅነውና ካላመነው ደግሞ ረድኤቱን (ረዳትነቱን) ልናገኝ አንችልም። የእግዚአብሔርን እርዳታ የሚፈልግ ምን ማድረግ አለበት? የፈጣሪ እርዳታ የማያስፈልገው በራሱ መኖር የሚችልስ ይኖር ይሆን? በፍጹም አይኖርም። በዚህም ምክንያት በእውነተኛው አምላክ የምናምን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በሃይማኖት እናየዋለን በጸሎት እናነጋግረዋለን፡፡ በዚህ ዓለም ሳለን ስለ እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ የምናስተውለው በሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ «ያለ ሃይማኖትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም» (ዕብ 11 ፥ 6) እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ። ሰው ፈጣሪ አለኝ ብሎ ካመነ ዘንድ ያለ ሃይማኖት መኖር አይችልም፡፡ እውነተኛ ሃይማኖት ለሥጋም ለነፍስም እንደሚጠቅም ቀጥለን እንመልከት፡፡
ይቀጥላል …… ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ።