በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ ዓሜን ።
ምስጢረ ሥላሴ

ምሥጢረ ሥላሴ ማለት ከአምስቱ አዕማደ ምስጢር አንዱ እና የመጀመሪያው ሲሆን ስለ ሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት ምስጢር የምንረዳበት ትምህርት ነው።
ይህውም ሥላሴ የሚለው ትርጉም
ሠለሰ ሶስት አደረገ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፤ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት ሲሆን የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሶስትነት ጥቅል መጠሪያ ስም ነው ስለዚህም ሥላሴ ብለን ስንጠራ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታች ነው።

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን

ዘፍ 1 ፥ 26 ። “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር አለ” ከዚህ ቃል በፊት እግዚአብሔርን የሚመስል ፍጡር መኖሩን የሚገልጽ ባለመኖሩ “በመልካችን…”የሚለው እግዚአብሔር የራሱ የሆነ ከአንድ በላይ መልክ እንዳለው ያስረዳል ። “በመልካችን..”የሚለው ሶስትነቱን(ከአንድ በላይ መሆኑን)“አለ” የሚለው ደግሞ አንድነቱን ይገልጽልናል ።

“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ 3 ፥ 22 ። እግዚአብሔር በአካልና በስምና በግብር ሶስትነት ባይኖረው ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” በማለት ይናገር ነበር ። “ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው ግን ብዙ ቁጥርን አመላካች በመሆኑ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።

ዘፍ 11 ፥ 7 ። “ኑ እንውረድና ቋንቋቸውን እንደባልቀው አለ” ይህ ቃል አንዱ ሌሎቹን ኑ እንደሚል እንረዳለን ። በዚህም እግዚአብሔር ለአምላክነት ሥራው የማንንም እርዳታ እንደማይፈልግ የሚታወቅ ሲሆን በውስጡ ከሁለት በላይ እንደሆነ አንዱ ሌሎቹን “ኑ” በማለቱ ያስረዳል ።

ዘፍ 18 ፥ 1 ። እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ ስር ለአብርሐም ተገለጠለት ። አብርሐምም ዓይኑን አነሳና ሶስት ሰዎችን አየ የሚለው እግዚአብሔር በሶስትነቱ በሰዎች አምሳል ለአብርሐም መገለጡን በቁጥር ሶሰት መሆናቸውን ያስረዳል ።
ኢሳ 63፥ 8 ።ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ በክብሩ ተምልታለች ይላል የህም እግዚአብሔር ሶስትነት ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል ።<እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይሳሐቅ አምላክ የያዕቆብ አምላክ ነኝ አለው ዘጸአት 3፥6
የሥላሴ ሦስትነት በሐዲስ ኪዳን።
ማቴ 16፥17 በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነውና እርሱን ስሙት አለ እግዚአብሔር አብ መሠከረ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወረደ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ባህር ሲጠመቅ ታየ።
ማቴ 28፥19 እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ ፣በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙር አድርጓቸው።
የእግዚአብሔር ሦስትነት ፤ እግዚአብሔር ፤ በስም ፤ በግብር ፤ በአካል ፤ ሦስት ነው ።

የስም ሶስትነት እንደምን ነው ቢሉ።
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመባል ይገለጻል ።
የአብ ፍቅር ፤ የወልድ ፀጋ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ፤ የሚለው ቃል ሶስትነቱን በግልጽ ያስረዳል ። 2ቆሮ 13 ፥ 14 ።
ስሙ (የወልድ) ፤ የአባቱ ስም ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ የተጻፈባቸው ። ራዕ 14 ፥ 1 ። ከላይ የተገለጹት የእግዚአብሔርን የስም ሶስትነት ያስረዳሉ ።
አብ ፤ በራሱ ሥም አብ ይባላል እንጅ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም ። ሶስቱም በየስማቸው ይጠራሉ ። ሃይ አበው ምዕ 11. ክፍል 1 ፡ 7 ።
“ሥላሴ” ማለት ሦስትነት ማለት ሲሆን ፤ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የሦስትነት ጥቅል ስም ነው ። “ሥላሴ” በምንልበት ጊዜ አብ ፤ ወልድ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፤ ማለታችን ነው ።

የግብር ሶስትነት

ግብር ሥራ ማለት ሲሆን ፦ በዚህ ክፍለ ትምህርት የእግዚአብሔርን የግብር ሦስትነት ስንል (አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ መሆናቸውን) እናያለን ።
አብ ማለት አባት (ወልድን የወለደ) ። ማቴ 3 ፥ 17 ።
ስራጺ ማለት መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ (ያስገኘ) ። ዮሐ 15 ፥ 26 ።
ወልድ ማለት ፤ ተወላዲ (ከአብ የተወለደ) ። ሉቃ 1 ፥ 35 ።
ዮሐ ፲፭ ፥ 26 ። ማለት ነው ።
የግብር ሶስነቱ የስሙን ሶስትነት ይገልጻል ። አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ (ሕይወት)፣ በማለት ። ይህ ማለት ግን አብ አባትና አስገኝ ፣ ስለተባለ ከአብና ከወልድ አይቀድምም አይበልጥም ፤ ወልድም ከአብ አያንስም ፤ ከመ ንፈስ ቅዱስ አያንስም ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ አያንስም ። ሁሉም እኩል በአንድነትና በሶስትነት ይመሰገናሉ ።

የአካል ሶስትነት

ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈሰ ቅዱስ ለየራሳቸው
ፍፁም (ሙሉ) ገጽ ፣ ፍፁም መልክ ፣ ፍፁም አካል ፣ አላቸው ።

ገጽ ማለት ፊት ሲሆን ፣ ከአንገታችን በላይ የሚታዩት የሰውነት ክፍሎቻችንን ዓይን ፣ ጆሮ ፣አፍንጫ ወዘተ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ።
መልክ በእያንዳንዳቸው የሰውነታችን ክፍሎች (እግር ፣ እጅ ፣ ራስ ፣ ፀጉር ፣ ዓይን ፣ ጆሮ…..) ተብለው ሲቆጠሩ ነው ።
አካል በአጠቃላይ ሙሉው የሰውነታችን ክፍል ነው ። የፍጡራን አካል የሚታይ ፣ የሚዳሰስ ፣ የሚመጠን ፤ የሚወሰን ፣ ሲሆን የሥላሴ አካል ግን ፤ የማይታይ ፣ በእጅ የማይዳሰስ ፣ በቦታ የማይወሰን ፣ በሁሉም ሙሉ ነው ። መዝ 138 ፥ 7 ።
የእግዚአብሔር የአካል ሶስትነት ። በማቴ 3 ፥ 16 ። እንደተገለጠው አብ በደመና ፣ ወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመሆን በግልጽ ታይቷል።

የእግዚአብሔር አንድነት

የእግዚአብሔር አንድነት በስም ፣ በግብር ፣ በአካል ፣ ብቻ ሲሆን በሌላው ሁሉ ለምሳሌ በባህርይ በህልውና ዮሐ 14 ፥ 8 ።
በፈቃድ ፣ በሥልጣን ፣ በመፍጠር… ፣ አንድ ነው ። ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በተለያየ ሥራና ደረጃ ተጽፎ ብናገኝም የስማቸውን የግብራቸውንና የአካላቸውን ሶስትነት ለመግለጽ እንጅ በአንዱ ሥራ ሁሉም አሉበት ። ዓለምን ፈጥሮ እየገዛ ያለ ፣ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነ ፣ አምላክ አንድ ብቻ ነው ። ኤፌ 4 ፥ 5 ።

ኩነት (ከዊን)

ኩነት ወይም ከዊን ማለት ሁኔታ ወይም መሆን ማለት ሲሆን ፣ ይህም በሰው ነፍስ ምሳሌ ይገለጻል ። ነፍስ አንዲት ስትሆን ሶስት ባህርያት (ኩነታት) አሏት ፤ እነሱም ፤
ልብ (ማሰብ)
ቃል (መናገር)
እስትንፋስ (ሕይወት) ናቸው ። ከሶስቱ ባህር ያት አንዱ ከተጓደለ ነፍስ የሚለውን ስም ልታገኝ አትችልም ።
ይኸውም ማለት አብ በልብ (ማሰብ)
ወልድ በቃል (መናገር) ፣ መን ፈስ ቅዱስ በእስትፋስ (ሕይወት) ሲሆን አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕይወት ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው ።
በእግዚአብሔርነቱ ፤ ልብ ፣ ቃል ፣ ሕይወት አለ ነፍስ ሶስት ባህርያት ቢኖሯትም አንድ እንደምትባል እግዚአብሔርም ሶስት ስም ፤ ሶስት ግብር ፤ ሶስት አካል ፤ ቢኖረውም አንድ አምላክ እንጅ ሶስት አማልክት አይባልም ። ዘዳ 6 ፥፬ ። ሚል 2 ፥ 10 ።

የእግዚአብሔርን አንድነትና ሶስትነት ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች
ፀሐይን ስንመለከት፣
አካል (መጠን) ፣ብርሃን ፣ሙቀት አላት ። በአካሏ አብ ፣ በብርሃኗ ወልድ ፣ በሙቀቷ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ፀሀይ ሶስት ሁኔታዎች ሲኖሯት አንድ ፀሐይ እንደሆነች እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
እሳትን እንመልከት፦
ለእሳት አካል ፣ብርሃን ፣ሙቀት (ዋእይ አለው።በአካሉ አብ፣በብርሃኑ ወልድ፣ በሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ።
ውሃን ስንመለከት ፦
ይዘት(ስፋት) ፣ እርጥበት ፣ ቅዝቃዜ አለው ።
በይዘቱ (በስፋቱ) አብ ፣ በእርጥበቱ ወልድ ፣ በቅዝቃዜው መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ ። ውሃ አንድ እንደሆነ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ሶስት ፤ ሶስት ሲሆን አንድ አምላክ ነው ።
ሌሎቹም በምሳሌነት የሚቀርቡ ፍጥረታት አሉ ።
ነገር ግን በምሳሌነታቸው ለማስተማር እንጅ የአምላክን ባህርይ የፍጡር ባህርይ ሊያስረዳ አይችልም ።
ብዙ ታላላቅ የሊቃውንት መጻህፍትን ስንመለከት ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖት አበዉ ክፍል አንድ (አብ አምላክ ነው ወልድም አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ። ነገር ግን ሶስት አማልክት አይባልሉም።አለ
ቅዱስ ኪራኮስ ዘአንጾኪያ አብ ለብቻው የሚሰራ አይደለም ወልድም ለብቻው የሚሰራ አይደለም መንፈስ ቅዱስም ለብቻው የሚሰራ አይደለም።
አብ የወደደውን ወልድና መንፈስ ቅዱስ ይፈጽማሉ ስራቸውም አንድ ነው ብሎ መስክሯል።
አባ ሕርያቆስ ዘብህንሳ በቅዳሴ ማርያም ላይ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ያስባሉ ይናገራሉ ይፈቅዳሉ ብሎ አንድነትን አስተምሮናል።
ቅዱስ ፊላታዎስ የተባለው ሊቅ በሐይማኖት አበው ክፍል ሁለት (ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ አብ ልባቸው ነው።
ለመንፈስ ቅዱስና ለአብም ወልድ ቃላቸው ነው።ለአብና ለወልድ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋሳቸው ነው ። በማለት የሥላሴን አንድነት እና ሶስትነት በሚገባ ገልፀዋል
ባጭሩ ለመግለጽ እንጅ የምስጢረ ሥላሴ ትርጉም ይህ ብቻ ነው ማለት አይቻልም።

የአብ በረከት የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ።
መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ጻድቅ ደበብ