ጾመ ጽጌ እንዴት ባለ ሥርዓት ይጾማል ይከበራል ?

መስከረም 26 – ህዳር 6 — ጾመ ጽጌ

የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

ጾመ ጽጌ እንዴት ተጀመረ ?!

የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፣ “አቡነ ዜና ማርቆስ የምሁርን ሕዝብ አስተምረውና አሳምነው ካጠመቁ በኋላ እንደገና ለማስተማር ወደ ይፋት ሄዱ፡፡ በዚያም ክርስቶስ ሥጋ ለብለሶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰለኛ ኃጢአት ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሣ እያሉ ሲያስተምሩ አንድ አይሁዳዊ ሰማ፡፡ ይህም አይሁዳዊ እንዴት እነዲህ እያለ ያስተምራል ሲል ተቃውሞ አቀረበባቸው፡፡ እርሳቸውም የብሉይና ሐዲስ ዐዋቂና ብልህ ስለነበሩ የሚከተለውን ጥቅስ እየጠቀሱ ያስረዱት ጀመር፡፡”

“ትወፅዕ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እምጒንዱ”፣ ትርጓሜውም “ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከግንዱም አበባ ይወጣል ያቆጠቁጣል” ማለት ነው፡፡ በትር አመቤታችን ድንግል ማርያም ስትሆን ጽጌ ደግሞ ከእርስዋ የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲሉ አቡነ ዜና ማርቆስ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 11፣1 ያለውን ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ዘርዝረው ባስረዱት ጊዜ አይሁዳዊው አምኖ ትምህርታቸውን ተቀበለ፡፡

አቡነ ዜና ማርቆስም ሐዲስ ኪዳን አስተምረው አሳምነው ካጠመቁት በኋላ አመነኮሱት፣ ስሙንም ጽጌ ብርሃን ምሁረ ኦሪት ስለ ነበር መጻሕፍተ ሐዲሳትን ለማጥናት ምቹ ሆነለት፣ ቀጥሎም ከርሳቸው ጋረ እየተዘዋወረ ወንጌል ያስተምር ጀመር፡፡

ይህንንም ከፈጸመ በኋላ እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ሃምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌ ደረሰ፡፡ አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር፡፡ ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው፡፡ አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም መስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ማኅሌት ጽጌ ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየበዓታቸው ይመለሱ ነበር፡፡

ይህም ማኅሌተ ጽጌ ድርሰት በሰምና ወርቅ የተደረሰ ሆኖ አበባን ሰም፣ ጌታንና እመቤታችንን ወርቅ እያደረገ ስለሚናገር ለሚያነበውና ለሚጸልየው እጅግ ያስደስታል፡፡

እንግዲህ ከላይ ከቀረበው የአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም ጀምረዋል፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ፡፡ ጥቂት መነኮሳትና አንዳንድ ምእመናንም በገዛ ፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ያዙ፡፡ በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል፡፡ ሴቱ ወንዱ፣ ትንሹም ትልቁም ይሰበሰባል፣ ማኅሌተ ጽጌ እየተዜመ፣ አስፈላጊ የሆነው በጸናጽል በከበሮ እየተመረገደና እየተወረበ እየተሸበሸበ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል፡፡ የጽጌ ጾም የውዴታ /የፈቃድ/ እንጂ የግዴታ አይደለም፡፡

የእመቤታችንን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት፣ ለራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም፡፡ የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፡፡ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፣ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!!!