ዐብይ ጾም

በታምራት ኃይሉ

ጾም ማለት ሰውነትን ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ መከልከል፣ ለሥጋ የሚመቸውን ነገር መተው ማለት ነዉ፡፡ ጌታችን መጾም ሳያስፈልገው የጾመው በጾም መሣሪያነት ዲያብሎስን ድል ታደርጋላችሁ ሲለን ነው፡፡  እርሱ ድል አድርጎታል ካልጾሙ ካልጸለዩ ሰይጣንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ጌታ አስተምሮናል፡፡ ጾም ፊትን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት እንደሆነ በሰብአ ነነዌ ታውቋል እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የተመለሱት በጾም ነውና፡፡ ኃጢአታቸው እጅጉን ገዝፎ ቅድመ እግዚአብሔር ስለደረሰ የጌትነቱ ቁጣ አስቀድሞ ከመምጣቱ በፊት ንስሐ እንዲገቡ መሐሪ እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ላከላቸው፡፡ ሕዝቡም የነብዩ ዮናስን ስብከት ሰምነተው በክፉ ሥራቸው ተጸጽተው ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለብሰው ጾሙ፣ ሕፃናትና  እንስሳትም የንስሐቸው ተካፋይ እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ በዚህ ጊዜ የፍጥረቱን መዳን እንጂ መጥፋቱን የማይወድ እግዚአብሔር ቁጣውን በትዕግሥት መዓቱን በምሕረት መልሶ በይቅርታ ጎበኛቸው ከተቃጣው መቅሠፍት አዳናቸው (ዮና  ፫ ፥ ፭-፲ )፡፡ ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት የተመለሱ ድኅነትን እንዳገኙ ሁሉ ያልተመለሱ ደግሞ ጠፍተዋል፡፡ ለምሳሌ ሰብአ ሰዶምና ሰብአ ገሞራ እንደ ነነዌ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ባለመመለሳቸው እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጥሎ አጥፍቶአቸዋል (ዘፍ ፲፱፡፳፫)፡፡ 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከሚጾሙት 7ቱ አጽዋማት አንዱና ትልቁ ዐብይ ጾም ይባላል፡፡ ይህ ጾም ዐብይ ጾም ፣ ጾመ ኢየሱስ ፣ ጾመ ሁዳዴ ፣ አርባ  ጾም በመባል ይታወቃል ፡፡

  • ዐብይ ጾም መባሉ ትልቅና ታላቅ ጾም መሆኑን ለማሳወቅና አምላካችን ለሰዎች በመጀመሪያ አብነት ለመሆን የጾመው ስለሆነና በቁጥርም ከሌሎች አጽዋማት ከፍ ስለሚል ነው፡፡
  • ጾመ ኢየሱስ መባሉ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ነው (ማቴ ፬፥፩)።
  • ሁዳዴ ጾም መባሉ ይህ ስያሜ የወጣዉ ሁዳድ ከሚለዉ ሲሆን ሁዳድ ማለት ሰፊ የእርሻ ቦታ ማለት ሲሆን ዐብይ ጾምም የሥላሴን ልጅነት ያገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ሰፊና ትልቅ ወደሆነዉ ካገኙት የማያጡት ወደ መንግስተ ሰማያት የሚያደርስ ሁሉም ምዕመን የሚጾመዉ ጾም በመሆኑ አባቶቻችን ጾመ ሁዳዴ ብለዉ ሰይመዉታል፡፡  
  • 40 / አርባ ጾም ይኸዉም ጌታ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔደ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ፣ ጸለየ ብሎ ቅዱስ መጽሐፍ በማቴዎስ ፬፤፪ እንደ ተጻፈ ጌታ አርባ ቀን የጾመዉ ጾም ስለሆነ ነዉ፡፡

ዐብይ ጾም ሦስት ክፍሎችና ስምንት ሳምንታት ያሉት ሲሆን እነሱም ፡-ሦስቱ ክፍሎች የተባሉት እነዚህ ናቸዉ፡፡

  • ዘወረደ ( ጾመ ሕርቃል )፡-ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ  ያለዉ ቀን ነዉ፡፡
  • የጌታ ጾም፡-ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣእና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለዉ 40 ቀን ነዉ፡፡
  • ሕማማት ፡- ይህም ጌታችን በአልአዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሣዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሥዑር  ያለዉ መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ነዉ፡፡ ይህም  7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነዉ፡፡  

የአብይ ጾም ስምንት ሳምንታት

፩- ዘወረደ

፪- ቅድስት

፫- ምኩራብ

፬- መጻጉዕ

፭- ደብረ ዘይት

፮- ገብርኄር

፯- ኒቆዲሞስ

፰- ሆሣዕና

፩- ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል)  ፡-

የመጀመሪያው የዐብይ ጾም መግቢያ እሑድ ዘወረደ ይባላል ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ በ641 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ ባሰራችዉ ቤተመቅደስ ዉስጥ ሲገባ ንግስቷ በክብር አስቀምጣው የነበረዉ የጌታችን የመድኃኒታችን  የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘዉ፡፡ ቢነካዉ አቃጠለዉ ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላዉን ንዋያተ ቅዱሳት ዘርፎ  60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋን አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየጉራንጉሩ ገብተዉ የተሸሸጉ ተሰብስበዉ ከ 14 ዓመት በኋላ በ628  ጩኸታቸዉንና የደረሰባቸዉን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰዉን የገደለ እድሜዉን በሙሉ ይጹም ስላሉ  እንዴት ላድርገዉ አላቸዉ እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን ብለዉ አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸዉ ጾሙን በሚገባ ጾመዉታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለንጉሥ ሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉ ሲቀበርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችዉ ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታዉ አስወጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢያት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በዉስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢያት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይል እንደሰጠኸዉ ለእኛም በኃጢያት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ግዜ ለንጉሥ ሕርቃል ህዝቡ ሱባኤ ይዞለታል ዛሬም እኛ ለቤተክስቲያን ከመቼዉም በላይ ልንጾም ልንጸልይ ይገባናል፡፡ ለሕርቃል የሰጠዉን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያዉ ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዢ የሆነዉ ዲያቢሎስ ነዉና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈዉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ ጾም ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ ለሥጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን የሆነ አንዱና ዋነኛዉ የጽድቅ እቃ ጦራችን ነዉ፡፡ሆኖም የጾም  ወቀት ሲመጣ አቀበት የሚወጡ ይመስል የሚፈሩትና የሚያማርሩት ሳይሆን እንኳን መጣልን ተብሎ በጉጉት የሚናፈቅ መሆን አለበት፡፡ በተለይ አሁን በቤተክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ በሚታየዉ አስቸጋሪ ፈተና እያንዳንዳችን ልባዊ ጾም በመጾም ልዑል እግዚአብሔር የጸሎታችን ምላሽ እንዲሰጠን እንማጸናለን፡፡

ጾም ፀሎታችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይቀበልልን አሜን፡፡

ይቀጥላል