በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን፤አግዐዞ ለአዳም፤ ሰላም፤ እም ይእዜሰ ኮነ/ይኩን፤ ፍስሐ ወሰላም።
በሃይማኖት ጸንታችሁ በጾም፣በጸሎት፣ በሱባዔ፣ በምጽዋት፣ በስግደት፣ በሕግ በአምልኮት ለእግዚአብሔር ስትገዙ እና ስታገለግሎት የቆያችሁ ክርስቲያኖች ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ እንኳ ለብርሃነ ትንሣኤው በጤና አደረሳችሁ።
መግቢያ
የትንሣኤው ትምህርት እጅግ ሰፊና ምሉዕ ነው። በዚህ መልእክት የምናስተላልፍላችሁ በዓሉን ለማስታዎስ ያህል በአጭሩ ነው። በመጀመሪያ ትንሣኤ የሚለውን ኃይለ ቃል ልብ አድርጎ መያዝ ይገባል። የሚነሣ ምን የሆነ ነው? ብሎ በመጠየቅ መጀመር ሙሉ መልእክቱን በአእምሮ ለማሳደር ይጠቅማል። ትንሣኤ የሚለው ቃል የውድቀት ተቃራኒ ነው። ትንሣኤ ወይም መነሣት የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን በአካለ ሥጋ፣ በነፍስ እና በመንፈስ ወድቆ ለተናሣ ሁሉ ይነገራል። በአካል ሥጋ ሰው ከተቀመጠበት፣ ከተኛበት፣ አዳልጦት ወይም መሰናክል አሰናክሎት ወይም ዕንቅፋት አንቅፎት ለወደቀና ከወደቀበት ለተነሣ ሰው ተነሣ ይባላል። በነፍስ እና በመንፈስ ደግሞ በኃጢአት ከወደቀበት በንሥሐ ሲነሣ፣ በድንቁርና ከወደቀበት በመንፈሳዊ እውቀት ትንሣኤ ልቡናን ሲነሣ፣ በእውቀቱ መንፈሳዊ ፍሬን በማፍራት እና እንደተማረው በመኖር ትንሣኤ ሕሊናን ሲነሣ፣ ፈተና እና መከራ ድርሶበት አዝኖ ተክዞ የነበረው አንገቱን ደፍቶ የነበረው ሲፅና ሲበረታ ተነሳ ይባላል። መደኑን አረጋግጡ «አይቴ እንከ ቀኖትከ ሞት = ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ኃይልህና ሥልጣነህ ወዴት አለ? ወአይቴ መዊዖትክ ሲኦል = መቃብርስ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ይዞ ማስቀረትህ ወደየት ነው?» እያለ በሞትና በመቃብር እየዘበተ ከኃጢአት ረቆ፣ በጽድቅ ደምቆ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አሸብርቆ ሲገኝ የትንሣኤ ልጅ ይባላል።
በዚህ መልእክት የምናበሥረው የሰው ልጅ በኃጢአት ወድቆ ከወደቀበት የሚያነሣው አጥቶ በራሱም መነሣት ተስኖት ለአያሌ ዓመታት ለሰፊ ዘመናት በሥጋው በመቃብር፣ በነፍሱ በሲኦል በመንፈሱም በኀዘን በትካዜ በጭንቀት ወድቆ ሲኖር ይህ ሁሉ የችግር ተሠሪ በክርስቶስ ትንሣኤ እንዴት እንደተወገደለት እና በክርስቶስ ትንሣኤ ደኅንነቱና ነፃነቱ እንዴት እንደተረጋገጠለት ነው።
የሰውን የወድቀቱን አስከፊነት እና እንዴት ካለ የመከራ አዘቅት በክርስቶስ ትንሣኤ በኩርነት እንደተነሣ በውል እንዲገባን ከውድቀት በፊት እንዴት ይኖር እንደንበር ማወቅ ጠቃሚ ነው።
የሰው ልጅ የሰባት ዓመት የገነት ቆይታ
ቅድመ ውድቀት አዳም እና ሔዋን በሰው አንድበት እንደሚገባ ተድርጎ ሊገለጽ በማይቻል ተድላ ደስታ ይኖሩ ነበር። ይህ የሚገባን ከወድቀት በኋላ በተሰማቸው ስብራትና በከበባቸው ኁልቁ ወመሣፍርት የሌለው መከራ ግራ ሲጋቡ እና የሚይዙትን የሚለቁትን በማጣት ሲሠቃዩ ከቅዱስት መጻሕፍት ስናስተውል ነው።
«ወበሱባዔ ቀዳማዊ ዘኢዮቤልዩ ቀዳማዊ ወሀለው አዳም ወብእሲቱ ሰብዐተ ዓመተ ውስተ ገነተ ኤዶም እንዘ እንዘ ይትቀነዩ ወይትዐቀቡ = በመጀመሪያው ኢዮቤልይ፣ በመጀመሪያው ሱባዔ አዳምና ሚስቱ በኤዶም ገነት ሰባት ዓመት ሲሠሩና ሕጉን ሲጠብቁ ኖሩ … ወኀሊቆ ፍጻሜሁ ለ፯ቱ ዓመት እለ ፈጸሙ በህየ ፯ተ ዐመተ ጥንቁቀ። ወበካልዕ ወርኅ አመ አሡሩ ወሠቡዑ መጽአ አረዌ ምድር ወቀርበ ኀበ ብእሲት =… በሁለተኛው ወር በ17ኛ ቀን እባብ መጥቶ ወደ ሔዋን ቀረበ። (ኩፋሌ 4፥14 እና 17)ይለናል።
ከእነዚህ የተወደዱ የተደላ እና የደስታ የፍሥሐ እና የሐሤት የሰባት ዓመት ከ1 ወር ከ17 ቀን ቆይታ በኋላ ደስታቸውን እና ምቾታቸውን የሚያጠፋ የሚያሳጣ ችግር ከራሳቸው ውስጥ በቀለ።
የሞት ልደት፤ ዕድገት እና ሞት
ሞት ኃይል አልቦ፣ ሥልጣን የለሽ፣ ጥቅም የለሽ ሆኖ ተፈጥሮል ይኖር ነበር። አዳም በሞት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። በመታዘዝ ተቆጣጥሮት ለመኖርም ሆነ ባለመታዘዝ በራሱ ላይ ሊያሠለጥነው በቁጥሩ ሥር ሊሆን ውሳኔውን እግዚአብሔር ለአዳም ትቶለታል። ወበእንተዝ በከመ በጌጋየ አሐዱ ብእሲ ቦአት ኃጢአት ውስተ ዓለም፤ በእንተ ይእቲ ኃጢአት መጽአት ሞት ላእለ ኩሉ ሰብእ = ስለዚህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባች። ስልዚችም ኃጢአት ሞት ገባ (ሮሜ. 5፥12) እንደተባለው ሞት ዓይኑን አፍጦ፣ ጥርሱን አግጦና ኃይል ነሥቶ የተገለጠው ሰው በፈጣሪው ላይ በመፀ ጊዜ ነው። የሰውን ልጅ በሕይወቱ የሚያስፈራው ትልቅ ነገር ሞት ነው። ከሞት በላይ በኑሮው ሰውን የሚያስፈራው ምንም ነገር የለም።
በመሆኑም ሁሉም ሃይማኖቶች የሞትን ተፅዕኖ እና በሰው ላይ የሚያደርሰውን ችግር ለመፍታት በአስተምህሯቸው ጥረት ያደርጋሉ።
እኛ ክርስቲያኖች ለሞት ዘላቂ መፍትሔ በሚሰጥ ሞትን በሚገደል ሃይማኖት እናምናለን። በክርስቶስ እመን፣ ምግባርን አስከትል፣ እንዲሁም ከኃጢአት ጋር ተጋደል ገነት ትገባለህ፣ ልጅነትህ ተመልሶልሃል በንሥሐ ተዘጋጅ እንጂ ሞት አያገኝህም እያልን ለሞት ተጨባጭ መፍትሔ እንሰጣለን። እውነተኛውና በቂው ትምህርት ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንዶቹ ለሞት ተደጋጋሚ ሥልጣን የሚሰጥ ስብከት ያራምዳሉ። ከእነዚህም አንዳንዶቹ እንደገና ትወለዳላችሁ፣ አንዳንዶቹም ሌላ ፍጥረት ሁናችሁ እንደገና ተፈጥራችሁ ወደዚህ ዓለም ተመልሳችሁ ትመጣላችሁ አንዳንዶቹም ለሞት መፍትሔ ሳይሰጡ በገነት ብዙ ሚስቶች የዘጋጁላችኋል በማለት የሞትን ክብደት ለማቃለል፣ ክፋቱን ለመቀነስ ሲሉ በተለያየ ጥበብ በተሠራ ትምህርት ለመፍታት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ቡዲዝምም፣ ሂንዱይዝምም ታኦይዝምም ሺንቶይዝምም ወዘተ ለመንፋሳዊ ችግርና ለሞት መፍትሔ አይሰጡም። ለኃጢአት ችግርና ለመንፈሳዊ ችግር ተጨባጭ መፍትሔ የሚሰጥ ክርስትና ከዚያውም ዘንድ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ነው።
ሞት የሰው ልጅ ሊቆጣጠረው የማይችለው ኃይል ነው። ሞትን ማንም ሊያስቆመው አይችልም። ሞትን ማንም ሊቋቋመው አይችልም። ሞትን ማንም ሊያስወግደው አይችልም። በሌላ መልኩ ሞት አያዳላም አስተካካይ እና እኩል አድራጊ ነው። ሁሉም ወደ አንድ መቃብር እንዲሄዱ ያደርጋል። በንገድ፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በሀብት፣ በዕድሜ ሳይለይ ሁሉንም በእኩል ወደመቃብር እንዲወርዱ ያደርጋል።
ሞት በዲያብሎስ አልተፈጠረም፤ ዲያብሎስ እንዲያውም የሞትን መኖር ለመደበቅ ሞክሯል። መጀመሪያ ሞት የተፈጠረው በእግዚአብሔር ነው፤ ሆኖም ሞት ያለ ኃይል በዕፀ በለስ ወስጥ ተሠውሮ ይኖር ነበር። ስለዚህ ሞት የመግደልን ኃይል የተጎናጸፈው ከኃጢአት ነው። ኃጢአትም ከሰው ተፀንሳ ተወልዳለች።
ሞትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው የሞትን መኖር ለሰው ልጅ የነገረው እግዚአብሔር ነው። ሰይጣን አይደለም። ሞት በአካባቢው ካሉት የገነት ዕፀዋት ውስጥ ዕፀ በለስን ተጠግቶ እንዳለ፤ ሆኖም ኃጢአት በመሠራት ኃይልን ካልሰጠው በቀር የመጉዳት አቅምና ችሎታ እንደሌለው በትክክል ለሰው ልጅ የነገረው እግዚአብሔር ነው። የሞትን የመጀመሪያ አፈጣጠርና በገነት የሆነ ቦታ እንደተቀመጠ ፈጣሪው ለአዳም እንዴት እንደነገረውና እንዳስጠነቀቀው ከቅዱስ መጽሐፍ እንመልከት።
ወአዘዞ እግዚአብሔር ለአዳም ወይቤሎ እምኩሉ ዕፅ ዘሀሎ ውስተ ገነት ትብልዕ = እግዚአብሔር አዳምን በገነት ካለው ዕፅ ሁሉ የተገኘውን ብላ ብሎ አዘዘው። ወእም ዕፅሰ ዘያርኢ ወያሌቡ ሠናየ ወእኩየ ኢትብላዕ እምኔሁ = በጎውን ክፉውን ከሚያሳውቀው ከዕፀ በለስ ግን አትብላ አለው። የፍጡር እና የፈጣሪ፣ የገዥና የተገዥ፣ የንጉሠ ነገሥትና የንጉሥ ተዋረድ ድንበር፣ የንጉሥና የእንደራሴ ምልክት ተደርጉልና። እስመ
በዕለተ ትብልዕ እምኔሁ ሞተ ትመውት = ከዚያ ዕፅ በምትበላበት ቀን የሞት ሞትን ትሞታለህና አትብላው አለው። ተብሎ እንደተጻፈው የሞትን ሞኖር ያስተዋወቀው እግዚአብሔር ነው።
ሞት በዚህ የአትክልት ቦታ በገነት ውስጥ አለ ነገር ግን አታድርግ ያልኩህን ጠብቀህ ከኖርክ ምንም አያደርገህም ገር ነው። ከሰማያዊ ነጉሠ ነገሥት በሚወርድልህ መመሪያ መሠረት የተሰጠህን ትእዛዝ ተቀብለህ ምድርን በሰማያዊ ሥርዓትና ባህል በማስተዳደር ፋንታ ብታምፅ እና ምድርን ከሰማያዊ ሥርዓተ መንግሥት ለይተህ ገንጥለህ ለብቻህ ይዘህ ለመኖር ብትሞክር፤ ያን ጊዜ ሞት ሕያው ይሆናል አንተ ኝ በፋንታህ ምውት ትሆናለህ ብሎት ነበር።
ሞት ወዲያው እንደተፈጠረ ነው የሞተ፤ ኃይልን እና ጉልበትን ያገኝው ነፍስ ዘርቶ እንዲነሣ ያደርገው የሰው ኃጢአት ነው። የኃጢአት ኃይሏ ደግሞ አትብላ የሚለው ሕግ ነው። ሰው የፈጣሪውን ትእዛዝ በጣሰ ጊዜ አትብላ ሞትን በእርግጥ ተሞታለህ የሚለውን የፈጣሪው የእግዚአብሔር ቃልና ማስጠንቀቂያ አቃሎ ብላ አትሞትም እንዲያውም እንደሱ ወደአምላክነት ከፍ ብለህ ዋናውን የሰማይ መንግሥት እና የሰማይ መንግሥት ቅኝ አድርገህ እንድታቀና የያዝካትን ምድርም ሁለቱንም ትገዛለህ ያለውን የዲያብሎስን ቃል ቅድሚያና ክብር ስጥቶ በተቀበለ ጊዜ እውነተኛ የባሕርይ ንጉሥ ቃልና ትሞታለ ተብሎ አስቀደሞ ያለቀው ፍርድ በአዳም ተፈፃሚ ሆነ። ፈጣሪው እንደነገረው አዳም ሞተ እንጂ ሰይጣን እንደነገረው አልከበረም። ይህ የአዳም ዓመፅ ለሞት ኃይል እና ሕይወት ሆነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ «ወቀኖቱሰ ለሞት ኃጢአት፥ ወኃይላኒ ለጢአት ኦሪት = የሞት ሥልጣኑ ኃጢአት ናት፣ የኃጢአትም ኃይሏ ሕግ ነው» ብሎ እንደተናገረው። (1ኛ ቆሮ. 15፥55)።
በዚህ መንገድ ሰው እንኳን ሰማይን ሊጠቅልል ሰው መሆንም ቀረበት። ከእርግማን እና ከሞት ሥልጣንና በታች ወደቀ። በክብር ከፈጠረውና ለብዙ ክብር ይመኘው ከነበረው ከፈጣሪው ጋር ተጣላ። መላእክትም ከገነት አስወጡት። ተመልሶም እንዳይገባ ገነት በሚንቀለቀል እና በሚገለባበጥ የንበልባል ሰይፍ ታጠረች። በሯም በአምላካቸው መንግሥት መደፈር በተቁጡና ለአዳም አስፈሪ በሆኑ መላእክት እንዲጠበቅ ተደረገ።
ወአውጽኦ እግዚእ እግዚአብሔር ለአዳም እምገነተ ተድላ ከመ ይትገበራ ለምድር እንተ እምኔሃ ወጽአ ወአኅደሮ ቅድመ ገነተ ትፍሥሕት ። ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወለሱራፌል ዘውስተ ዕደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት = ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም ካስወጣው በኋላ፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ ዘፍ. 3፥23።
አዳም እግዚአብሔርን እንቢ ብሎ ከሰይጣን ጋር በተወደጃ ቀን ወዲያ በዚያው ቀን ተጎዳ። እንግዲህ የሰይጣንን ምክር ስምቶ እግዚአብሔርን ከዙፋኑ አውርዶ እራሱን ሊተካ በመሞከሩ እንኳን አምላክ ሊሆን ሰው መሆኑም ቀረና ፈጥረታት ሁሉ ለፈጣሪያቸው በማደር የተፈጥሮ ሕጋቸውን ጠብቀው በአዳም ላይ ተነሡበት።
የሰውን ልጅ ወድቀት ያመጣበት ከሰማያዊ መንግሥት እንደራሴነትና ወኪልነት በማፈንገጥ ነፃ መንግሥት መሆኑን ለማወጅ ያደረገው እምቢተኛነት ነበር። የእንቢተኛነቱ ወጤት ምን አስከተለበት የሚለውን በጥቂቱ ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት።
የሰው ልጅ የእንቢተኛነቱ ውጤት
❖ አስፈላጊ ብርሃንን አጥቷል፤ ጨለማ ውጦታል።
❖ የንጉሡን እና የመንግሥቱን ባለሟልነት አጥቷል ማለትም የእግዚአብሔርን ፊት እና የፍቅር ድምፅ፡፡
❖ ስለዚህ አዳም ስለራሱ ራሱ የሚወስን ሆነ፤ የራሱን የወደፊት አካላዊ እና መንፈሳዊ ጉዳይ ብቻውን በኃላፊነት ወሳኝ ሆነ። የመንፈስ ቅዱስን አብርሆት አጣ።
❖ ሕይወቱን እግዚአብሔር አውርዶ ሞትን በላዩ ላይ በሾመ ጊዜ አስቀድሞ እንደተነገረው ወዲያውኑ የመንፈስ ሞትን ሞተ።
❖ የልጅነት ሥልጣኑን አጣ፣
❖ የገዢነት ሥልጣኑን አጣ፣ በአርአያው፣ በምሳሌው እና በመልኩ የተፈጠረ በምድር ላይ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነበረና እግዚአብሔርን የሚያስመስሉትን ጸጋዎች ሁሉ አጣ።
❖ ገነትን እና በገነት የነበረውን መዐዛዋን፣ በረከቷን ሁሉ አጣ፣ አንድም ነገር አላንጠለጠለም ባዶ እጁን ወጣ። አጣ፣ ጎዳና ተዳዳሪ፣ ከቤቱ የተባረረ አውታታ ከርታታ ሆነ።
❖ ሰላም እና ደስታን ዕረፍትን አጣ፣ ክፉን የማያውቅ የነበረው አዳም ይህን ሁሉ መከራ ተሸክሞ የኃዘን እና የመባዘን፣ የሁከት እና የመቅበዝበዝ አድካሚ ኑሮውን ተያያዘው።
❖ አዳም ከሞት ጋር ተፋጠጠ፤ አልቻለውም። በመንፈስ እርሱን ወዲያውኑ የገደለው ሲሆን በአካል ጭምር መግደልን በልጁ በአቤል አሳየው። የሚወደውን ልጁን አቤልን በመቀማት ሥልጣኑን በማሳየት አሳዘነው። በፈቃዱ ፈጣሪው እያስጠነቀቀው እንቢ ብሎ በራሱ ላይ የሾመው ሞት ከሕይወቱ ከቤቱ አልወጣ አልላቀቅ ብሎት ተሠቃየ። በመቃብር እና በሲኦል ገዛው፣ወደመቃብር እና ወደ ሲኦል አወረደው።
❖ አዳም ታረዘ ልብስ ተቸገረ፤ ከዕርቃንነት ጋር ታገለ፤ በሚስቱ እራቃን አፈረ እሷም በእርሱ እርቃን አፈረች ። ተራቆተና ልብስ ፈለጋ ደከመ፤ ቢችግረው ለአንድ ቀን እንኳ የማይሆን የቅጠል ልብስ አዘጋጀ። የእርሱ አቅም የሚችለው እስከዚህ ነበርና። ሰው ከፈጣሪው ሲለይ ይህን ያህል ደካማ ነው። አዳም ከሐፍረት ሸሺቶ ለመደበቅና ለማምለጥ ሞከረ አልቻለም። ከብዙ ጉድና ችግር የሸፈነው የፈጣሪው ጸጋ ተወስዷልና የሚያስጠጋውና የሚተባበረው አላገኘም።
❖ አዳም ከፍርኀት ጋር ተናነቀ። የፈጣሪውን ደምፅ በገነት በሰማ ጊዜ ተደብቆ ለማምለጥ ሞከረ ግን ወደየት? መፍንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክሮ ከሽፎበታልና ጭነቀው። ዓለም በምልዑ እርሱ ከሥልጣን ሊያወርደው ሙከራ ባደረገበት በንጉሡ በእግዚአብሔር ስንዝር የተለካች ናት፤ሁሉም ነገር ሲወደውና ሲያከብረው ሳለ እርሱ ግን በከዳው በፈጣሪው በእግዚአብሔር መዳፍ ውስጥ ነውና ሙከራው ሁሉ ከንቱ ነበር።
❖ ስደት አዳም ከገነት ተባረረ፣ መልአክ ተልኮ አስደነገጠው፣ ከገነት አስወጣው ተብሎ ታዞ የመጣ መልአክ ከገነት አስወጥቶ ተመልሶ እንዳይገባም በነባልባል ሰይፈ አጠረበት በሩንም አጥብቆ ዘጋበት።
❖ በዚህ ሁኔታ ኃጢአት ለሞት ይህን ሁሉ ኃይል እና ሥልጣን ሰጠው። ስለዚህ ሞት ኃጥአተኞችን ይገድላል።
የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት አስፈላጊነት
አዳም በገዛ ኃጢአቱ የመግደልን ኃይልን እና ሥልጣን ለሞት በማቀበል ከላይ የተጠቀሱትን እና ተዘርዝሮ የማያልቀውን ሁሉ መከራ ወደ ራሱ ከመጋበዙም ባሻገር ከእርሱ የሚወልደው ልጁ የልጅ ልጁ ሁሉ ለሞት እንደተፈጠረ የራሱ የአዳም ኃጢአት ምልክት እየሆነበት ይወለድ ጀመር።
ስለዚህ ሞትን የሚያሞተው እና የሚገድለው ሥልጣኑን ኃይሉን የሚቀማው ንጹሕ ሰው ያስፈለገን ንበር እና ንጹሐ ባይርይ ክርስቶስ ሞተልን። እርሱ ሰለ እኛ ሞቶ ጠላታችን ሞትን ገድሎ ከራሱም ካአባቱም ከመንፈስ ቅዱስም ጋር አስታረቀን።
የሞት ኃይል ኃጢአት ነው የሚለውን ካሰረገጥን ዘንድ፤ «በከመ ውእቱ ኢገብረ ኃጢአተ ወኢተረክበ ሐሰት ውስተ አፉሁ = እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም» (1ኛ ጴጥ. 2፥22)። እንደተባለው ለመያዝና ለማስቀረት ኃይል የሚሆነው የመግዛት ሥልጣን የሚሰጠውን ኃጢአትን በጌታችን ዘንድ ስላላገኘ ሞት በክርስቶስ ላይ አንዳች ማድረግ አልቻለም። ምክያንቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ የሞትን የኃይል ምንጭ ኃጢአትን ባለማድረግ መትቶታል አድርቆታል።
ለሞት ሕይወት የምትሆን ኃጢአትን የሚያለማት ዲያብሎስ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የሞት ኃይሉ፣ ብርታቱና ጎልበቱ የሚሆን ኃጢትን ባለማድረግ አድክሞ ሊይይዘው በሞከረም ጊዜ ከመቃብር በታች አውርዶትና ረግጦት በድል አድራጊነትና በግርማ ተነሥቷል።
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ሞተ ወኬዶ ለሞት። ለእለ ውስተ መቃብር ወሀበ ሕይወተ ዘለዓለም ዕረፍተ = ሲተረጎም ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ሞቶ ሞትን ገደለው። በመቃብር ለነበሩትም ሕይወትና እና የዘላለም ዕረፍትን ሰጠ። ማለት ነው። እንዲህ እያልን ለመዘመር አብቅቶናል። እርሱም አንተ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት = አንተ ትንሣኤና ሕይወት ነህ፤ መባል ይገባዋል። (ዮሐ. 11፥25)።
የክርስቶስ የሞቱ ዓላማ
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለሰው ሞት ቅጣት ምትክ መሆን ነው፣ የአመፅ መንፈስን ማጥፋት ማለት ((ኃጢአትን)) ከሰው ልጆች ውስጥ ለመፋቅ ነው፣ በሰው እና በሰው በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ ለማድረግ ነው፣ የሰማያዊ መሪና አስተዳዳሪ (የመንፈስ ቅዱስ) መኖሪያን ለማፅዳት ነው፣ በሰማይ ያለውን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የመንግሥት ሥርዓት እንደገና እንድትቀበል ዓለምን ለማዘጋጀት ነው። የሞቱ አላማ የሰው ልጅ ያጣው እና በጣም አስፈላጊው የሆነው የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የሰማይ በጎ ተጽዕኖ በምድር ላይ እንደገና እንዲጠናክር ነበር፡፡ ጌታችንም ቅዱሳን ሐዋርያት ጽሎት አስተምረን ባሉት ጊዜ «ትምጻእ ምነግሥትከ፣ ወይኩን ፈቃድከ፣ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር = መንግሥትህ ትምጣ በሰማይ ያለ ፈቃድህ የሚደርግባት የሚፈጸምባት ትሁን፤ ምድር በሰማያዊ ሕግ ትመራ ሰማይን ትምሰል» ብላችሁ ጸልዩ በማለት የመንግሥቱን ብሔራዊ መዝሙር አስተምሯቸዋል።
የሰው ልጅ ያጣውና የሚያስፈልገው ነገር ገን ያለ ክርስቶስ ሞትና የድል ትንሣኤው የማያገው የነበረው ነገር ብዙ ነው። መንገሥቱን፣ መንፈስ ቅዱስን፣ የእግዚአብሔርን አባትነት፣ ገነትን፣ የመንፈስ ቅዱስን አመራር፣ የምድርን ፍጥረታት የመቆጣጠር እና የማስተዳደር ሥልጣኑን፣ማንነቱን ሁሉ አጥቶ ነበር። ይህ ሁሉ በትንሣኤው የተጎናጸፈው ሀብት አሁን እንደገና ተኖበታል።
ከሞት ማዶ ያለ መንግሥት
ምድራውያን መንሥታት የሚገዙን እስኪሻሩ ቢበዛ ወደመቃብር እስኪወርዱ ወይም እኛ እስከምንሞት ነው። ወሰኑ መቃብር ነው:: የእግዚአብሔር መንግሥት ከሞት ተሻግሮ በዜጎ ላይ መገዛቱን ቀጥሏል:: ከእንግዲህ ወዲህ በእግዚአብሔር መንግሥት ሞት ዜጎችን ከንጉሣቸው ከክርስቶስ መለየት አይችልም ፡፡ የጌታ ትንሣኤው በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ንጉሥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነውና፡፡
የጌታ ትንሣኤ ሰላምን ይሰጣል:: ብንኖርም ብንሞትም የእግዚሔብር ነን ማለት ትልቅ ስላም ነው:: ስንሞት ለጊዜው ከዚህ የለም ከሞት ማዶ ወዳለው ሀገር ተሻግሯል እንባላለን እንጂ ሞቷል አንባልም። ሞት በጌታችን ስለ ተገደለልን በእኛ ላይ ሥልጣን የለውምና። ከዚህ ስንታጣ ከዚያ እንገኛለን ከዚያ ስንታጣ ከዚህ አለንና ትንሣኤው ሰላምና ዕረፍትን ይሰጠናል።
ሰው ያጣው ሰማያዊ የምድር ውክልና ወደላቀ የፍቅሩ ለጅ መንግሥት ስለመሻገሩ
ከሰደት እና ከወድቀት ባነሣን በክርስቶስ የቤዛነት ሥራ እንደገና የመንግሥት ልጆች ለመሆን እንደበቃን የትንሣኤው እና የትንሣኤያችን ሰባኪ ቅዱስ ጳውሎስ «ወአድኀነነ እምኩነኔ ጽልመት ወአግብአነ ውስተ መንግሥተ ወልዱ ፍቁሩ = ሲተረጎም እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን
ሥርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን በእውቀት ለድንቁርና ከመገዛት፣ በወንጌል ለኦሪት ከመገዛት፣ በልጅነት ለሰይጣን ከመገዛት ልጁ ወዳጁ ወደሚያወርሳት ወደመንግሥተ ሰማይ የመለሰን እግዚአብሔርን አመስኙት። (ቆላ. 1፥13-14) ብሎ እንደተናገረ ሰው በፈጣሪው ምህረትና ቸርነት ከውድቀት፣ ከሞት ተነሥቶ እንደገና ወደዙፋኑና ወደመንግሥቱ ተመልሷል።
የተበላሸው ስለመስተካከሉ የተወሰደው መንግሥት ስለ መመለሱ ከዚሁ ዝቅ ብሎ ከቁጥር 18 እስከ 21 ላይ «ወበከመ በጌጋየ አሐዱ ብእሲ ተኮነነ ኩሉ ዓለም ከማሁ ወካዕበ በጽድቀ አሐዱ ብእሲ ይጸድቅ ኩሉ ዕጓለ እመሕያው። እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ዓለም ሁሉ እንደ ተፈረደበት፥ እንዲሁም ደግሞ በአንዱ ሰው ጽድቅ ሁሉም ይጸድቃል። ቁጥር 18። በከመ አንገሠቶ ኃጢአት ለሞት። = ኃጢአት ሞትን እንዳነገሠችው፤ ከማሁ ታነግሦ ለጽድቅ፣ ጽጋሁ ለእግዚአብሔር ውስተ ሕይወት ዘለዓለም በእንተ እግዜእነ ኢየሱስ ክርስቶስ = እንዲሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጸጋ ጽድቅን ለዘላለም ሕይወት ታነግሠዋለች» ሲል የምሥራቹን ነገረን። በአንዱ ሰው በአዳም ምክኛት በዚህ ዓለም ሠልጥኖ የነበረው ባርነት፣ ሞት፣ መርገም፣ ድህነት፣ ሥቃይ መከራ በአንዱ ሰው በዳግማዊ አዳም በክርስቶስ ተወግዶ በምትኩ ጽድቅ፣ በረከት፣ ድኅነት ልጅነት፣ ክብር፣ ነግሧል።
የትንሣኤው ትምህርትና ዘመናችን
ከላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደተረዳነው በክርስቶስ ቤዛነትና መሥዋዕትነት ከሞትና ከመቃብር አልጠን የትንሣኤ ልጆች እንድንሆን በእግዚአብሔር በኩል የቀረብን ነገር የለም። በውድ ልጁ በኩል ሁሉም ተደርጎልናል።
ይሁን እንጂ ዓለማችንን ስንገመግመው የክርስቶስ ቤዛነት፣ የከፈለው መሥዋዕትነት በቤዛነቱ፣ በሞቱ ይልቁንም በትንሣኤው ያስገኘው ክብርና የመለሰው የእግዚአብሔር ልጅነት ተቀባይ እና ወራሽ አላገኘም። የሰው ልጅ አሁንም በምግብ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጸጋ እና መንግሥት እየራቀ ይጋኛል። የገዛ ሆዱ ከባልጀራውም ከፈጣሪውም ጋር ደጋሜ እያጣላው ይገኛል። በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘውን የጽድቅ ብኩርና በኀላፊ፣ በጠፊ በጊዜያዊ እንጀራ እየሸጠው ይገኛል። የሰው ልጅ ልቡናው እንደ ገና ስለሸፈተ የክርስቶስ ትንሣኤ ባሰገኘለት ጸጋና ሀብት መጠቀም አልቻለም። አሁንም የቆጡን ለማውረድ የሚያደርገው ስግብግብነት የብብቱን እያስጣለው በአሳዛኝ ውድቀት ላይ ይገኛል። እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ሀሳብ ከመብልና ከመጠጥ ያለፈ መሆኑን «የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም» (ሮሜ. 14:17) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ያስጠነቅቃል።
እግዚአብሔር እና ሰብአዊነት የተለዩት እውቀት /ሳይንስ፣ ሞራል የተለየው የንግድ እንቅስቃሴ፣ ተስማሚነት /Conformity/ የአዳምን ዘር ከሃይማኖት ከሞራል ከሰባዊነት ከግብረ ግብነት እያራቀው እንደገና ወደ ሞት እያጋዘው ይታያል።
የትንሣኤ ልጆችና የሞት ልጆች
እንግዲህ ሞት፣ የፍርኀት፣ የኀፍረት፣ የፃዕር፣ የስደት፣ የኩነኔ፣ የመርገም፣ የርኩሰት የጉስቁልና የድህነት የውርደት ሠራዊትን ይዞ ሰውን እንዲከበው ኃይልና ጎልበት የሆነው ኃጢት ነው። ኃጢአት በክርስቶስ መሥዋዕትነት ይልቁንም በትንሣኤው ተመቶ እንዳልነበረ መደረጉን እንደ ደመና የሚከቡን ምስክሮች ያረጋግጡልናል።
ይሁን እንጂ ሁሉ እንዲሞት የአዳም ኃጢአት ምልክት ሁኖበት የሚወልደና የውርስ ኃጢአት ይኖርም አሁንም በግልና በቡድን በሚሠራ ኃጢአት፣ አመፅና በደል ምክንያት የሰው ልጆች መደብ ውጥቶላ ቸዋል። የእግዚአብሔር ወይም የትንሣኤ ልጆች እና የዲያብሎስ ወይም የሞት ልጆች ተብለው በሁለት ተመድበዋል።
ዲያብሎስ ማነው? ከፈጣሪው በላይ የሚያውቀ የለምና ፈጣሪ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎ ነፍሰ ገዳይና ሐሠተኛ ነው ብሎ ነግሮናል።በዚሁ መሠረት ነፍሰ ገዳዮችና ሐሰተኞችም የበኩር ልጆቹ ናቸው። ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ ገዳይ፣ አስገዳይ አገድዳዳይነቱን አላቋረጠም።
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጠላት እንኳ በሚሞት አርአያነትና በትንሣኤው ኃይሉን እና ሥልጣኑን ለመስበር፣ ለማፈረስና ለመደምሰስ መጥቶ ሲያስተምር በነበረበት ጊዜ በከንቱ ሊገድሉት የሚፈሉትን ከሰውነት እና ከእግዚአብሔር ልጅነት ወጥተው ከምን ደረጃ ላይ እንዳሉ «እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና» ሲል ባልወለዳቸው እና ባልፈጠራቸው በነፍሰ ገዳይ፣ ሐሰተኛ የሐሠት አባት በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር መውደቃቸውን ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 8፥44)።
የእግዚአብሔር /የትንሣኤ ልጆች እና የሞት /የዲያብሎስ ልጆች የሚለዩባቸው ነጥቦች።
ንጹሕ፣ ቅዱስ፣ በጌታችን ዘንድ የተውደደ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያይቱ መልእክቱ በምዕራፍ 3፥10 ጅምሮ እንደሚከተለው ለይቷቸዋል።
1) የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።
2) ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፣
3) ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።
4) ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።
5) ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።
6) እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።
7) ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?
8) ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። ይላል።
ማጠቃለያ
የተወደዳችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን፣ በትንሣኤው ኃይልን እና ተጨባጭ ተስፋን ያገኛችሁ ኦርቶዶክሳውያን ሆይ እራሳችንን እንመርምር፣ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ አካባቢያችን የምናይበት፣ የዓለምን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሰ የምንመዝንበት፣ ሕይወታችንን የምንመረምርበት መሣሪያ ፍጽሞ የለም። በዚሁ መሠረት በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መነፅርነት የግል ሕይወታችንን፣ አካባቢያችንን፣ ሀገራችንን፣ አሕጉራችንን፣ በጠቅላላው ዓለማችንን ስንመለከተው ሁሉም ከትንሣኤ ልጅነት ወጥተው የሞት ልጆች ሆነዋል። ወንድሙን ማለትም እንደ እርሱ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን ሰው ሁሉ የሚጣላ ነፍሰ ገዳይ ከሆነ የሚገድል ምን ስም ይገኝለታል! በሀገራችን ከጥላቻ አልፎ ንጹሐንን መጨፍጭፍ እና በጅምላ በዶዘር ማዳፈን እየተለመደ እና ባህል እየሆነ መምጣቱ ከጠራውና ከነጠረው ከእግዚአብሔር ቃል አንፃር እንዴት ይታያል? ሰባት ጊዜ መላልሰው ካጠሩት ወርቅ ይልቅ በጠራው የእግዚአብሔር ቃል እያንዳንዱ ሰው ሕይውቱን ቢመረምር የማን ልጅ እንደሆነ ሊያውቅ ይችላል። ከትንሣኤ ወገን ወይስ ከሞት ወገን ነኝ ብሎ ራሱን መርምሮ ከየትኛው ጎራ እንደተሰለፈ አስተውሎ ተስተካክሎ የትንሣኤውን በዓል ቢያክብር ክብርና ልዕልና፣ ልማት እና ዕድገት
ሊያስገኝ በተቻለው ነበር። አሁን ግን ኢትዮጵያውን በእርስ በርስ ደም መፋሰስ ከትንሣኤው በረከት እና ብርሃን ወጥተው የሚገኙበት ዓመት ስለሆነ ያሳዝኛል። የ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ትውልድ በገዛ ወንድሙ ደም ቀየውን እና ምድሩን ሁሉ እያመከነ ስለሆነ የወንድሙን ደም የተቀበለችና የጠጣች ምድር ኃይሏን ማለትም በረከቷን እንደ ከለከለችው እንደ ቃየል ተቅበዝባዥ እና ተንከራታች ሁኖ እንዳይቀር ያሠጋል።
አንዲት እናት ኢትዮጵያ አምጣ የወለደቻቸው ወንድማማቾች፣ የአንዲት ሀገር ልጆች ከጥላቻ አልፈው ሞትን ባህል እያደርጉት እና ግፍን እንደ ልማት እና ዕድገት እያዩት መጥተዋል። ይህን የሚፈጽሙት ሁሉም በትንሣኤው ባለቤት ስም ይጠራሉ። ነገር ግን በግብር የሞት ወዳጆችና ወገኖች መሆናቸውን በዕለት ከዕለት ድርጊታቸው እያየናቸው ነው። የሰላም እና የአንድነት ተምሳሌት በሆነችው በኢትዮጵያ ምድር በትንሣኤው ሰሞን ፣ እርስ በርስ የሚባላው እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ወጋናችን በጌታችን ትንሣኤ ከተገኘው እውነተኛ ደስታ እና ብርሃን ርቆ መገኘቱ የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል ድባብ አበላሽቶ ይገኛል።
ከትንሣኤ ጋር በተገናኘ አንድ ነግር ልብ ማለት ይገባናል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ መልካም እና በጎ ፍጹምም በረከት መቀብል ካልፈለግን እና ከገፋነው ባለቤቱ መልሶ ይወስደዋል፣ አስገድዶ አይጭንብንም። በውድ ልጁ ሞት፣ ሞታችንን አሙቶታል። ሕይወቱን፣ ጽድቁን፣ መንግሥቱን ልጅነትን መልሶልናል። በተለይ በትንሣኤው የሰጠን የሰላም ሀብት ካልፈለግነው ወደመጣበት ይመለሳል፣ በትንሣኤው የተገኘው ሰላም ወሰን አልነበረውም «ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው» (ዮሐ. 20፥19-23)። ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው በትንሣኤው በዝቶና ተትረፍርፎ የተሰጠን ሀብት ሰላም ነው።
በዚች አጭር አንቀጽ ውስጥ ሰላም ለእናንተ ይሁን የሚለው ቡራኬ ትንሣኤውን ለምናምን ሁሉ ተደጋግሞ ሲሰጠን እናያለን። ይሁን እንጂ ሰላም ከማይቀባላትና ከማይገባው አካባቢ አትቆይም፣ አትውልም አታድርም። ሰላምን ከልብ በመቀብል ነው እንጂ ደጋግሞ ስለ ሰላም በማውራት እና በመስበክ ጥቅሟን ማግኘት ፈሬዋንም መመገብ አይቻልም። ይህንን ማስረገጥ ብንፈልግ «በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ» (ማቴ. 10፥133)። ሲል ጌታችን ተናግሯል። ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ የድል አድራጊ ንግግሩ ትኩረት እና ቁልፍ የሆነው «ሰላም ላኩልክሙ የሚለው» የሚለው የበረከት ቃል እና የድል አዋጅ በአንድ ቅዳሴ መካከል ከ14 ጊዜ በላይ ይጸለያል። ይታወጃል፣ ይሁን እንጂ እስካሁን በዐውደ ምህረቱም አካባቢ የሚጠበቀውን ያህል አላበበም።
ከቤተ ክርስቲያን ወጣ ብለን ስንቃኝም ስለ ሰላም የሚሸልሙ ድርጅቶች፣ እንዲሁም አዘውትረው ስለ ሰላም የሚያወሩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አያሌ ናቸው። የዚያኑ ያህል ሰላም በእጅጉ እየጠፋ ነው። በትንሣኤው የተገኘውን እውነተኛውን ሰላም ለመቀብል ፈቃደኛ መሆን እንጂ ስለ ሰላም ጧት ማታ ከአንገት በላይ ማውራቱ የግብዞች ከንቱ ድጋም ነው። እንግዲህ የትንሣኤው ብርሃን በሀገራችን እና በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ያለውን ደቅድቅ ጨላማ ያብራልን፤ አሜን፣ ይሁን ይደረግልን።
የእኛን ሞት ወስዶ የእርሱን ሕይወት የሰጠን፣ በትንሣኤው ከወደቅንበት ያነሣን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ምስጋና ይድረሰው ትክክል የሚሆን ዘሬም ዘወትርም ለዘላለሙ።
አባ ሕርያቆስ
የኢጣሊያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።
ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/ም