{ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ }
ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች።ኢሳ 11፥1
በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን (የግንቦት ልደታ) የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ‘ ‹‹የመመኪያችን ዘውድ፣ የንጽሕናችንም መሰረት›› ያላት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተወለደችበት ነው፡፡ *ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ድንግል ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች (ኢሳ 7፡14)›› ብሎ ትንቢት የተናገረላት ያቺ ድንግል በዚህች ዕለት ተወለደች፡፡ ይህች ቀን ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹ የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች (መዝ 44፡9)›› ብሎ የተናገረላት ንግሥት የተገኘችባት ዕለት ናት፡፡
*ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ ‹‹ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አስራ ሁለት የክዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት (ራዕ 12፡1)›› ብሎ የመሰከረላት የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ የእርስዋም ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን ሲገለጽ የነበረ ነው፡፡ [የድንግል ማርያም ልደት በነቢያት አንደበት? እግዚአብሔር የዝማሬና የትንቢት ጸጋን ያበዛለት ክቡር ዳዊት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥርወ ልደት አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት ተገልጾለት፧ {መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን} መሠረቶችዋ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው።
በማለት ትንቢት ተናግሯል፦
መዝ 86÷7‹‹የተቀደሱ ተራሮች›› ያለውም የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ከሆኑት ከተቀደሱት ከኢያቄምና ከሐና የምትወለድ መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡ ‹‹የእመቤታችን ማርያም ትውልዷ ባባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፤ በናቷም በኩል ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው፤ የአባቷ ስም ኢያቄም ነው፤ የእናቷም ስም ሐና ነው፡፡
¶ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ፡ ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡ ኢሳ 11፡1 ለዚህ ነበር ከዐበይት ነቢያት ወገን የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስም ጥበብንና እውቀትን ተገልጾለት ስለሚመጣውም ነገር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ‹‹ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ /ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል/›› በማለት ታላቅ ትንቢትን አስረግጦ ተናገረ፡፡ ይህች በትርም ዛሬ የቃል ኪዳን ምልጀዋ ይድረሰን እና ልደቷን በታላቅ ድምቀት እያከበርን የምንገኘው ከእሴይ ዘር የተገኘችው በዚህች ዕለት ነው።
*(ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ከእሴይ ሥር የተገኘሽ መዓዛሽ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ›› በማለት በውዳሴ አመስግኗታል፡፡ ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ (መዝ 131፡13)›› የተባለልን የአባቶቻችን ልጆች እኛም እንዲሁ እያልን እናመሰግናታለን፡፡
የእመቤታች ልደት በሊባኖስ ስለመሆኑ፦
አስቀድሞ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት /ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከአማና ራስ ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች/›› መኃ 4÷8 በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የዚህ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸው የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ትንቢቱም ሲፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በ15 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡
ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን የተናገረው ቃልም መፈጸሙን ሲገልጽ ‹‹….የአናብስት ልጅ አልኩሽ፡፡ ሰሎሞን እንዲህ ሲል እንደተናገረ፡- ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ ተራራ ነዪ፤ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ፤ ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው፡፡››
በማለት አመስጥሮታል፡፡ እመቤታችንም በሊባኖስ ተራራ እንድትወለድ ምክንያት የሆነው በማሕፀን ሳለች የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሳቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ስለነበር ሐናና ኢያቄም ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሄዱ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ስለነገራቸው እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
የድንግል ማርያም ልደት በራዕይና በምሳሌ ከትንቢቱ በተጨማሪም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በራዕይና በምሳሌም አስቀድሞ የተገለጸ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ከእርሷ ሰባት ትውልድ አስቀድሞ ለነበሩት ደጋግ ሰዎች እንዲሁም ለእናትና ለአባቷ የተገለጹት ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻሕፍት በሰፊው ሰፍረው ይገኛሉ፡፡
ሰባተኛዪቱ እንቦሳ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየሁ (ቴክታ) በቅድስና የሚኖሩ ነገር ግን መካን የነበሩት ቴክታና ጴጥርቃ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አይተው በሀገራቸው መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) አለና ሂደው ነገሩት፡፡ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም፤ እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም ‹‹ረከብኩ ስእለትዬ፤ ረከብኩ ተምኔትዬ›› / የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ/ ሲሉ ‹‹ሄኤሜን››አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ ከኢያቄምና ከሐናም በጨረቃ የተመሰለች ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡
ፀዓዳ ርግብ ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በማሕፀኔ ስታድር አየሁ (ቅድስት ሐና) ኢያቄምና ሐና መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም ተገልጾላት ለባለቤቷ ለኢያቄም ‹‹ብእሴሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ /ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብቶ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ፡፡›› ብላዋለች፡፡ የዚህ ራእይ ምስጢርም ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው::
ከሰባተኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ (ቅዱስ ኢያቄም) በተመሳሳይ ኢያቄምም በሕልሙ ያየውን ለባለቤቱ ለሐና ‹‹እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ /ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ብሎ በሕልሙ የተገለጸለትን ነግሯታል፡፡ የዚህም ራዕይ ምስጢር ዖፍ የተባለው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፡፡ ኢያቄም ‹‹ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ የሚያጠይቅ ሲሆን ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ባህርይው፣ ምልአቱ፣ ስፍሃቱ፣ ርቀቱ፣ ልእልናው፣ ዕበዩና መንግስቱ ናቸው:፡
የድንግል ማርያም ልደት በሐዲስ ኪዳን ሊቃውንት የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ትንቢተ ነቢያትንና ወንጌልን በማጣጣም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት አመስጥረው አስተምረዋል፤ አመስግነዋል፤ ተቃኝተዋልም፡፡ የእርሷን ልደት እጅግ ብዙ ሊቃውንት በስፋትና በጥልቀት ያመሰጠሩት ሲሆን ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች (ቅዱስ ያሬድ) ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት ‹‹ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ/ ማርያምስ (ማርያም ግን) ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡›› በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ስለ ሥርወ ልደቷ ‹‹እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ… ሐረገ ወይን/ ሥሮቿ በምድር ጫፎቿም በሰማይ ያሉ…የወይን ሐረግ›› በማለት የተወለደችው በምድር ከነበሩት ኢያቄምና ሐና መሆኑን የወለደችው ግን ሰማያዊውን ንጉሥ እንደሆነ በማመስጠር ዘምሯል፡፡
*የብህንሳው ሊቀ ጳጳስ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ} ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› በማለት የድንግል ማርያም ጽንሰትና ልደት እንዴት እንደነበር በድርሰቱ አስፍሮታል፡፡ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት የሚላት የሁላችን እናት ድንግል ማርያም በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሳ ከዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ ግንቦት 1 ቀን ተወልዳለች፡፡ እርስዋም ስትፀነስ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከጥንተ አብሶ ፡ጠብቋታል፤ ኀጢአት አልነካትም፡፡ ይህንንም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በኃጢአት በተከበበ፣ መርገም በሞላበት ዓለም ውስጥ ከኃጢአት ከበደል ርቃ (ተለይታ) እንደ ጌዲዮን ጸምር በንጽህና የጠገኘች ንጽህት ዘር መሆኗን ሲያስረዳ *የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር (ኢሳ 1፡19)፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ጠቢቡ ሰሎሞን ንጽህናዋን በትንቢት መነጽር አይቶ “ወዳጄ ሆይ፣ ሁለንተናሽ ውብ ነው፣ ምንም ነውር የለብሽም፡፡ ሙሽሪት ሆይ ከሊባኖስ ነዪ፡፡” (መሓልይ 4፡7-16) በማለት በንጽህና በቅድስና ያጌጠች፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልነካት፣ የድህነታችን ምክንያት፣ የንጽህናችን መሰረት የሰው ባህርይ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲዋሀድ ምክንያት የሆነች ንጽሕት የሰርግ ቤት ድንግል ማርያም በሊባኖስ የመወለዷን ነገር አስቀድሞ የቀርጤሱ ቅዱስ እንድርያስ የከበረ ስለሆነው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ታላቅነት ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌው በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል፤ የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ ዕለት (ጌታ) መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነው፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡ በእውነት የእርሷ ልደት የልዑል ማደሪያው መቅደስ የተሰራበት ዕለት ነውና ሁላችን እናከብረዋለን፡፡ በዚህም ዕለት ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም/ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ›› እያልን እንዘምራለን። ይህችን የልዑል ማደሪያ እናቷ ሐናና አባቷ ኢያቄምም በእጅጉ ተደስተው በተወለደች በስምንተኛ ቀኗ ስሟን ‹‹ማርያም›› ብለው ሰይመዋታል፡፡
የእመቤታችን የልደት በዓል አከባበር አባታችን አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ፣ ንስሃ በገባ ጊዜ አምላካችን ጌታ እግዚአብሔር የድህነት ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ቃል ኪዳኑም “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም አዳም 5500 ዘመን የሕይወት ምክንያት የሆነች የልጅ ልጁ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአብራኩ ከተከፈሉ ቅዱሳን ልጆቹ የምትወለድበትን ቀን ተስፋ እያደረገ ኖረ፡፡ የእመቤታችንን የድንግል ማርያምን የመወለዷን ዜና ተስፋ በማድረግ “ሴት” ይላት የነበረውን ሚስቱን ሔዋንን በእመቤታችን ምሳሌነት “ሔዋን”፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ብሎ ሰየማት፡፡ (ዘፍ. 3፡ 20) ዳግማዊ አዳም የተባለ ክርስቶስም የአዳምን ተስፋ በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ እውነተኛዋን ሔዋን (ዳግሚት፣ አማናዊት ሔዋንን) ድንግል ማርያምን በዮሐንስ ወንጌላዊ በኩል ለሕያዋን ምዕመናን ሁሉ እናት አድርጎ ሰጠ፡፡ (ዮሐ. 19፡26) ይህን የከበረ ምስጢር የማይረዳ “ክርስቲያን” እንዴት ያሳዝናል!? እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን የቀዳማዊ አባታችንን የአዳምን፣ እንዲሁም በዳግም ተፈጥሮ ያከበረንን ዳግማዊ አዳም የተባለ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ተቀብለን “የሕያዋን ሁሉ እናት” ድንግል ማርያምን ልደቷን
በፍፁም ደስታ እናከብራለን፣ ከተወደደ ልጇ ምሕረትን ትለምንልን ዘንድም ወደ እርሷ እናንጋጥጣለን፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለን ምዕመናን ከጌታችን ልደት ቀጥሎ በታላቅ ድምቀት የምናከብረው የልደት በዓል የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት ቀን ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል (ሉቃ 1፡14)›› ከተባለ የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ የሚያስደስት ይሆን?! የነቢያቱ ትንቢት የተፈፀመበት፣ የታየው ራዕይም በገሀድ የተከናወነበት፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡ ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም በንጽህናዋ በቅድስናዋ
ተደንቀው “እህትነ ነያ/እህታችን እነኋት” ብለው ያመሰግኗታል፡፡ በዘመናችን ያሉ የሰዎች ልደት በድምቀት የሚከበር ከሆነ ለሰው ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ምንኛ ሊከበር ይገባው ይሆን?! ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡ የሕይወት ክርስቶስ እናት ዛሬ ተወልዳለችና፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትዉፊት መሰረት ሐና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር እመቤታችንን ወለዱ፡፡ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ይህንን ትዉፊት በመያዝ በዓሉ ከቤተ በቤክርስቲያን በያሬዳዊ ዝማሬ በማህሌት ፣ በቅድሴ በንግስ ከመክበራችን አልፎ ክርስቲያን ህዝባችን ከቤተሰብ ዘመድ ፣ ከጎረቤት ጋር ባንድ ላይ ዝክር በመዘከር ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡ ስለዚህ እኛም ቤተ ክርስቲያን ባቆየችን ሥርዓት መሰረት በቀናች በተዋሕዶ እምነት ፀንተን በምሕረቱ ያልተለየንን አምላካችን ብቻ እያመሰገን የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን ድንግል ማርያምንም እየተማፀን ልናከብረው ይገባል፡፡ የእመቤታች የድንግል ማርያም የእናትነት ፍቅሯ የቃል ኪዳን በረከትዋ አማላጅነቷ አይለየን ።
አምላካችን እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችን ;ኦርቶ ዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን: ተዋህዶ እምነታችን ከፈተና ይጠብቅልን ዓሜን።
የጽሑፍ አስተያየቶች