ምሥጢረ ቊርባን
ቊርባን ማለት ቃሉ ከሱር የተወሰደ ሲሆን፣ መስዋዕት ማለት ነው።
እንዲሁም ቊርባን ሙሉ ትርጉሙ ለአምላክ የሚቀርብ መንፈሳዊ መባዕ ፣ ስጦታ፣ አምኃ፣ ማለት ነው። አንድም ሥጋውና ደሙ የተሰጠን በነፃ ያለ ዋጋ በችሮታ ነውና ቁርባን ስጦታ ይባላል።
ምሥጢረ ቁርባን ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ በሥጋው በመሞቱ የዓለምን ኃጢአት ያስወገደበት፥ የዘላለም ሕይወትን ያስገኘበት የመዳናችን መሠረት፥ የጸጋችን ሁሉ ምንጭ የሆነውን የቅዱስ ሥጋውንና የክቡር ደሙን የማዳን ስራ የምንማርበት ታላቁ የሃይማኖታችን ትምህርት ነው። በቤተክርስቲያን የምሥጢራት ሁሉ ማሰሪያው ቅዱስ ቁርባን ነው። አማኞች ምሥጢረ ሥላሴን ምስጢረ ሥጋዌን ከተማሩና ከአመኑ ምሥጢረ ጥምቀትን ከፈጸሙ በኋላ በቅዱስ ቁርባን ይታተማሉ። ክርስቶስ መሥዋዕትም፣ መስዋዕት ተቀባይም፣ መስዋዕት አቅራቢም፣በመሆኑ ሊቀ ካህን ተብሏል። ሊቀ ካህንነቱንም፣ ሶስቱንም በአንድ ጊዜ በመፈጸም በቃልም በተግባርም አስተምሮናል ዕብ.፯፥ ፳-፳፰ እንደ መስዋዕትነቱ በመስቀል ላይ ሥጋው ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር ማቅረቡ፣ እንደ ሊቀ ካህንነቱ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅርበላቸው ብሎ ሰውን ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። እንደ አምላክነቱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ የጥልንም ግድግዳ አፈረሰ። የተራራቀውን አቀራረበ ይህም ነገር የቁርባንን የምሥጢር ትርጉም ያስረዳናል። ይህ ማለት በአንድ በኩል ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት፥ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፣ የምንዋሐድበት አንድ የምንሆንበት ምሥጢር ነው።እንዲሁም ካህኑ ኅብስቱን በጻሕል ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ በጸሎተ ቅዳሴ እንዘ ነአኩተከ ይረስዮ የሚለውን የጸሎተ የቅዳሴ ክፍል እየጸለየ በባረከው ጊዜ ኅብስቱ ተለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ሥጋ መ፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆንበትና እኛም የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ይህንን የክርስቶስን ሥጋና ደም የምንቀበልበት በመሆኑ ምሥጢር ይባላል፡፡
ምሥጢረ ቊርባን አራስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት እነሱም
ምሳሌው፣
+አመሰራረቱ፣
+የሚያስገኘው ጸጋ (ጥቅሙ)
+ቅድመ ዝግጅትና ድህረ ጥንቃቄ
=> ምሳሌው
ምሳሌውን በምናይበት ጊዜ ከኦሪት ብዙ የተለያዩ አብነቶችን እናገኛለን። በብሉይ ኪዳን ዘመን ለኃጢአት ስርየት በየዓመቱ የበግና የፍየል ጠቦት ይቀርብ ነበር በአጠቃላይ በምኩራብ የተሰዋዕ እንሰሳት ሁሉ በአዲስ ኪዳን በቤተክርስቲያን ለሚሰዋው የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር። በየጊዜው የኃጢአት ሥርየት መሥዋዕት ማቅረብ በሕገ ኦሪት የታዘዘ መንፈሳዊ ስርዓት ነበር። በኦሪት ዘመን በደል የፈጸመ ሰው ለኃጢአቱ ካሣ የሚሆነውን እንስሳ ይዞ ወደ ቤተመቅደስ ያቀርባል፡፡ካህኑም በእንስሳው ራስ ላይ እጆቹን በመጫን በደሉንና ጥፋቱን ወደ እንስሳው ያስተላልፋል። ከዚያም ምንም በደል የሌለበት እንስሳ ታርዶ ለመሥዋዕት ይቀርባል ዘሌዋ ፬፦፩ ይህም ምሳሌ ነው። ስለ በደላችንና ስለ ኃጢአታችን ካሣ ቤዛ ሆኖ በእኛ ምትክ የተሠዋልንን ክርስቶስን ያመለክታል። ለዚህ ነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም በዕለተ ዓርብ፣ ስለ ዓለሙ ድኀነት የተሠዋውን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን፣ አማናዊ በግ ያለው። ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየሐትት ኃጢአተ ዓለም ዮሐ፩፦፳፱ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ በማለት ይገልጸዋል። በኦሪቱ የነበረው ስርዓት ለእያንዳንዱ ሰው ለኃጢአት ማስተስርያ የሚሆን አንዳንድ ጠቦት ያስፈልጋቸው ነበር፣ የአዲስ ኪዳኑ አማናዊው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለዓለም የተሰዋ በመሆኑ መድኃኔዓለም ይባላል። ይህን ሲያስረዳ ነው ቅዱስ ዮሐንስ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ ሲል የተናገረው። ብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን አምሳል ወይም ጥላ እንደመሆኑ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ለእኛ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ የአማናዊው መሥዋዕት (ምሥጢረ ቁርባን) ምሳሌ በዘመነ ብሉይ የነበረ መሆኑን ብዙ መጻሕፍት ይናገራሉ። በዘመነ ኦሪት ከቀደምት አበው መካከል ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል ተብሎ የተነገረለት የሰላም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ በቀራንዮ ኮረብታ ላይ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ያሉት አባቶች ያቀርቡት እንደነበረው መሥዋዕት ሳይሆን በኀብስትና በወይን ይሠዋዕ ነበር፡፡
አበ ብዙኀን አብርሃም ኮሎዶጎሞርን አሸንፎ ሲመለስ ይኸው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ኅብስትና ወይን ይዞ ተቀብሎታል። የመልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዐ በረከት፣ የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ሲሆን መልከ ጼዴቅ ደግሞ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። ዘፍ. ፲፬፦፲፮ ዕብ ፯ ፦፩- መዝ ፻፲፦፬
=>በኦሪት ተመዝግቦ እንደምናገኘው፣እስራኤል በምድረ ግብፅ ለ፬፻፴ ዘመን ያህል በባርነት ሲማቅቁ ከኖሩ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ በነቢዩ ሙሴ መሪነት ምድረ ግብፅን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ከሞተ በኵር ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አላቸው። ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁንላችሁ። የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁንላችሁ በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ይውሰድ የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን። በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት። የእስራኤልም ማኀበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጎበኑን ይቅቡት። በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፡፡ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ ነገር ግን ከራሱ፣ ከጭኑ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። ከእርሱም እስከ ጠዋት አንዳች አታስቀሩ። እስከ ጠዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። እስራኤል ከሞተ በኵር የዳኑበት ተባት በግ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናል በማለት ጽፎአል። ዘጸ ፲፪፦፩-፳፱፣ ፩ቆሮ፮፦፯
=> የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በሚጓዙበት ጊዜ በምድረ በዳ ምንም የሚላስ፣ የሚቀመስ፣ በአጡበት ጊዜ መሪያቸው ሙሴን አስጨነቁት፡፡ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት መና ከደመና ወርዶላቸው፣ ያንን ተመግበው፣ ከረሃብ ድነዋል። ለእስራኤል በምድረ በዳ ከደመና የወረደላቸው መና የጌታ ሥጋና ደም ምሳሌ ሲሆን፣መናው የተገኘበት ደመና ደግሞ ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሰው የሆነባት የድንግል ማርያም ምሳሌ ነበር።< አንቲ ውእቱ ደመና እንተ አስተራይኪ ለነ ማየ ዝናም እንዲል >ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፣እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ። ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። በማለት ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ መድኃኒት ሲል መናው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ መሆኑን አስተምሮአል። ዮሐ ፮፦፵፱
አመሰራረቱ
መስዋዕት ማቅረብ የተጀመረው በአዳም ጊዜ ሲሆን ከአዳም እስከ ሙሴ የተነሱ አበው ሁሉ በህገ ልቦና ለእግዚአብሔር መስዋት ይሰው፣ ቁርባንን ያቀርቡ ነበር። መስዋዕታቸው ከእንሰሳ ቁርባናቸውም ከእህልና ከአትክልት ማለት ከስንዴ እህል፣ ከወይን ፍሬ፣ የሚቀርብ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ። አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ።ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ ተብሎ ተጽፎአል ዘፍ ፬፦፪
በሕገ ልቡና መስዋዕት በማቅረብ የሚታወቀው ሌላው ጻድቅ ኖኅ ነው። ኖኅ በእግዚአብሔር ጻድቅ ሆኖ በመገኘቱ ስምንት ነፍሳትን ጨምሮ ከንፍር ውኃ የዳነ ሰው ነው። ከመቶ አምሳ ቀናት በላይ በመርከብ ቆይቶ እግዚአብሔር ውጣ ሲለው ወጣ ኖኅ እግሩ የብስ እንደረገጠ በመጀመርያ ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረበ፣ እግዚአብሔርም መስዋዕቱን ተቀብሎ ድጋሚ ምድርን በንፍር ውኃ ላያጠፋት ቃልኪዳን ገባለት። ዘፍ ፰፦፩−፳፭ ፣ ፱፦፱−፲፪ ከላይ እንዳየነው መልከ ጼዴቅ ያበረከተው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከትን ጨሮ ብዙ ቅዱሳን በሕገ ልቡና መስዋዕት ሲሰው ኖረዋል።
ሕገ ኦሪት እንደተሰጠች ካህናት መስዋዕትን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ለሙሴ መታዘዙ አይዘነጋም በመሆኑም መሥዋዕተ ኦሪት ሰውን ከወደቀበት ማንሳት ስላልቻለ ይህን የኦሪት መስዋዕት በመሻር ሰውን ከሞትሞት የሚታደግ አማናዊ መሥዋዕተ አስፈልጎአል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አማናዊዉ ቅዱስ ቁርባን ሲያስተምር ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ይላል፣ ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን፣ የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። በዚህ ላይ መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው። ቀጥሎ፦ እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኦሪት መስዋዕት መሻርና ስለሐዲሱ መስዋዕት አስፍቶ አስተምሯል። ዕብ ፲፦፩-፱
በመሆኑም ይህ አማናዊ ቅዱስ ቁርባን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ቊርባንን በምሴተ ሐሙስ መስርቶታል።ወኀረየ እምውስቴቶሙ ፲፪ተ ሐዋርያተ አንሶሰወ ምስሌሆሙ ወአርአዮሙ ሥርዓተ ምሥጢር ዘቁርባን፣ ከሚከተሉትም አስራ ሁለትን መረጠ ከነሱ ጋር ተመላለሰ የቁርባን ምሥጢርንም አሳያቸው። እንዲል ቅዳሴ ሠለስቱ ምእት ሐሙስ ምሽት በአልዓዛር ቤት እራት ከበሉ በኋላ ከእራት ተነስቶ ሥርዓተ ቁርባንን ሠራ። በወንጌል እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ <ሥጋዬ ነው>አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው። እንዲህም አለ ይህ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው። ማቴ፳፮፦፳፮ ዮሐ፲፫፦፬- ስለሆነም የሐዲስ ኪዳን አማናዊው መስዋዕት(ቅዱስ ቁርባን) ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ በጸሎተ ሐሙስ በበዓለ ፋሲካ እንደመሰረተው ቅዱሳት ወንጌላውያኑ ያስረዳል።
ማቴ ፳፮ ፦፩ ማር ፲፬ ፦፩ ሉቃ ፳፪ ፦፩ ፩ ቆሮ ፲፩ ፡
በበላችሁ ጊዜ ሞቴን ትናገራላችሁ ብሎ ለሐዋርያቱ እንዳቀበላቸው እኛም እንዲሁ በቅዳሴያችን መካከል ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ አቤቱ ሞትህን እንሰብካለን እናስባለን፣ እያልን እንጸልያለን እንዘምራለን። አንዳንድ መናፍቃን ሰዎች በቃሉ መሰረት ሞትክን እናስባለን ስንል ስጋወደሙ መታሰቢያ ይመስላቸዋል። ግን አይደለም። ሊቃውንት ሲያስተምሩ ወበከመ ኩሎን ትምህርታት ዘተጽህፋ ለነ ከመጵርስፎራ ወወይን ዘይሰየሙ በጻህል ወበጽዋዕ ሥጋሁ ወደሙ ለአማኑኤል አምላከነ በአማን ነአምን። ወመናፍቃን ይጸውኡ ሥጋሁ ወደሞ ከመ ድራረ ክርስቶስ ውእቱ ወንህነሰ ኢንጸውዖ ድራረ ከማሆሙ። አላ ንብሎ ሥጋሁ ወደሙ እስመ ነአምን ከመ መጠዎሙ እምድህረ ተደሩ እንዘ ይትናገሮሙ እንዘ ይብል ”ዝንቱ ውእቱ ሥጋየ ወዝንቱ ደምየ ለሐዲስ ኪዳን” አኮ ይቤሎሙ ድራርየ ሉቃ ፳፪፥፳። ዮሐ፲፫፦፬ ሃይ አበ
በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደተማርነው በጻህል ያለው ሥጋውና በጽዋ የቀረበው ደሙ አማናዊ ስጋውና ደሙ እንደሆነ እናምናለን። መናፍቃን ግን የጌታን ሥጋና ደም እራት ነው ይላሉ። እኛ ግን አበው እንዳስተማሩ ከእራት በኋለ እንዳቆረባቸው እናምናለን። ሥጋው ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው እንደሆነ እናምናለን። አበው እንዳስተማሩን ለመታሰቢያ ሳይሆን ከርሱ ጋር ሕብረት እንዲኖረን እንዲሁም አዳኝ ስለሆነ ነው እንጂ።
ከመዝ ነአምን ወከመዝ ንትአመን ከመዝንቱ ኀብስት ዘንፌትቶ፣ሥጋ ክርስቶስ ውእቱ ዘነሥአ እምወለቶሙ ለዕብራውያን፣ ወካዕበ ነአምን ከመ ዝንቱ ጽዋዕ ደመ መለኮት ውእቱ ዘውኀዘ እምገቦ በግዑ ለእግዚአብሔር።እንዲህ እናምናለን፣ እንዲህም እንታመናለን ይህ የምንፈትተው የክርስቶስ ሥጋ እንደሆነ ዳግመኛም ይህ ጽዋዕ የእግዚአብሔር በግ ከሚሆን የፈሰሰ ደመ መለኮትእንደሆነ እናምናለን። ቅዱስ ቄርሎስ በመጽሐፈ ቅዳሴ ገጽ ፫፹፮ ቁጥር ፺፱ እንዲሁም በዚሁም መጽሐፍ እንደተጻፈው፣ ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ ከመብከ ንህየው ዘለኩሉ ዓለምን ወለዓለም ዓለም። ያንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ ስጠን። በዚህም ጵርስፎራ(ሥጋው ደሙ)አድነን ለዓለም ሁሉ በምትሆን በአንተ ለዘለዓለሙ ሕያዋን እንሆን ዘንድ በማለት ተጽፎ እናገኛለን ። እራሱ ክርስቶስ በቃልም፣ በተግባርም፣ ሥጋየን የበላ፣ ደሜንም የጠጣ፣ የዘለዓለም ሕይወት አለው።እያለ ያስተማረንን ትምህርት እናምናለን እንመራበታለን።እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ቅዱስ ቊርባን መታሰቢያ ሳይሆን የጌታ ሥጋ መሆኑን በግልጽ በመልእክቱ ጽፎልናል። ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።ሰው ግን፣ ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ። ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ ግን የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና ቆሮንቶስ ፲፩፦፳፯–፴ ለዚህ ነው፣ ቤተ ክርስቲያናችን ምዕመናኖችዋ ከመቁረባቸው በፊት በትምህርተ ንስሐ እራሳቸውን እንዲፈትኑ፣ እራሳቸውን እዲመረምሩና በቀኖና ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዲጠይቁ የምታደርገው። ከላይ በመግቢያ እንደጠቀስነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ። ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል። እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው ብሏል። ዮሐ ፮፦፶፩ ዳሩ ግን ልባቸው በአለማመን የተጎዱ አይሁድ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? በማለት ትምህርቱን ሊቀበሉት አልቻሉም። ሁሉን ቻይ የሆነ ጌታ፣ ዘመን በማይሽረውና በማይለውጠው አማናዊ ቃሉ አስቀድሞ በአጽንዖት እንዲህ ብሎ አስገንዝቦናል። እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፣ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ስለዚህ ማሰብ ማለት ሥጋውና ደሙን ስንቀበል መድኃኒታችን ለእኛ ድኅነት ሲል ከቤተልሔም ዋሻ እስከ ቀራንዮ ኮረብታ የደረሰበትን ጸዋትወ መከራ ሕማሙን፣ ግርፋቱን፣ስቅላቱን፣ሞቱን፣ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እንድናሰላስል እንድናስተውል ለማስረዳት ነው። ማሰብ፣ ትክክለኛ የቃሉ ትርጉም ከላይ የተገለጸው ለመሆኑ፣ የሐዋርያውን ትምህርት <በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ> ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡፡ ይህን <እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ> ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ በማለት ያረጋግጥልናል። ሥጋውን ደሙን በምንቀበልበት ጊዜ ሁሉ የጌታችንን መከራውን ሕማሙንና ሞቱን በልባችን ውስጥ ስሜት ይፈጥርብናል፣ እናሰላስለዋለን፣ እናለቅሳለን። እንዲሁም ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠንን የአምላካችን ፍቅር በኀሊናችን ሰሌዳ ተሥሎ እስከ ዕለተ ሞታችን እንዲኖር ቅዱስ ቁርባን ታላቅ ማኀተም መሆኑን በማስገንዘብ የዘላልም ሕይወት እንዲኖረን ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሐሙስ መስርቶታል።
የሚያስገኘው ጥቅም
በምሥጢረ ቍርባን የሚገኙ ጸጋዎች ወይም የሚሰጠው ጠቀሜታ ቅዱስ ቍርባን ሰውንና እግዚአብሔርን አንድ ያደርጋል፣ ያዋሕዳል ማለት የምንቀበለው ሥጋ የእርሱ ስለ ሆነ ከእርሱ ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን በኅብረት እንኖራለን።
ይህም ማለት እኛ በእርሱ፥ እርሱ በእኛ ይኖራል ማለት ነው። ይህንንም በትምህርቱ ጌታ እራሱ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” በማለት አስተምሮናል። ዮሐ ፮÷፶፮
ከጌታችን ከአምላካችን ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እና ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ይኖረናል ከላይ ። ፩ቆሮ ፲ ፥፲፮
ፍጹም የሆነ የኃጢአት ስርየት (ድኅነት) እናገኛለን ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል እንዲል ፩ኛ ዮሐ፩፦፯
ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በአዳምና ልጆቹ ላይ የመጣው የኃጢአት ሞት ሰውን ከፈጣሪው ጋር አራርቆ፣ባለዕዳ አድርጎት፣ ዲያብሎስ ሰልጥኖበት ይኖር የነበረበት የመከራ ዘመን ቀላል አልነበረም። ሰውና እግዚአብሔርን ያራራቀ ዲያብሎስን ድል የሚነሳ፣ ፍጹም ስርየተ ኃጢኣት የሚገኝበትና ሰማያዊ ዜጋ መሆን የሚቻለው፣ በቅዱስ ቁርባን ነው።ስለዚህ ነው ምስጢረ ቁርባንን ሲመሠርት ጌታችን ይህ ደሜ ነው ለብዙዎች የኃጢአት ሥርየት የሚፈሰው በማለት ያስተማረው።
የሰው ልጅ በመብላት ያጣውን ገነት ዳግም በመብላት እዲገባ ሲል በሚበላ አደረገው። ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሰማያዊና መንግስተ ሰማያት መግቢያ የሕይወት ምግብ ሲናገር፣ በልዐት እምዕፅ፡በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት፣ ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ ከፈለነ ንብላዕ እምዕፀ ሕይወት፣ ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚኣነ መጽአ ወአድኃነነ አይ ልቡና፣ ወአይ ነቢብ፣ ወአይ ሰሚዕ፣ ዘይክል አእምሮ ዝንቱ ምሥጢር እንዲል።
ሔዋን እፀ ሕይወትን በልታ ያዘጋችውን ገነት ከድንግል ማርያም የተገኘው የሕይወት ምግብ ኢየሱስ ክርስቶስን በልተን ለመግባት በቃን። ምን ልቡና ነው? ሊናገሩትም ለሰሚው አስደናቂ መሆኑን በሚገርም ሁኔታ ይገልጸዋል። በሚበላ ሲባል ግን ከምድራዊ ምግብና ከኦሪት መስዋዕት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን አማኞች ሊረዱት ይገባል።
ይህንንም ቅዱስ ሕርያቆስ በአማን ቁርባን በማለት ይገልጸዋል።መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቍርባን ነው። በበግ፣ በጊደርና በላም፣ እንደነበረው እንደ ቀደሙ አባቶች መስዋዕት አይደለም። ፈቃዱን ለሚሠሩ፣ ልቡናቸውን ላቀኑ፣ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው። ስሙን ለሚክዱ፣ ለዓመፀኞች ሰዎች ግን የሚባላ እሳት ነው። እሳታውያን የሚሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል ሊነኩት የማይቻላቸው በእውነት እሳት ነው። ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን፣ ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፣ እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና።
+ እክል ያጸንዕ ኃይለ ሰብእ ወቅብ ለአብርሆ ገጽ> እንዲል
ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል እንዳለ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር ፻፫፥፲፭ መንፈሳዊ ምግብ (ምሥጢረ ቁርባንም) የአማኞች ነፍስ በጣዕመ ጸጋ የተመላ፣ መንፈሳዊ ደስታንና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ያደርጋል። መብልና መጠጥ ከሰዉነታችን ጋር እንደሚዋሀድ በጸጋ ተዋህጃችኋለሁ ሲል በመብልና መጠጥ አደረገው። ሥጋዊ ምግብ ለቁመተ ሥጋ ለአጽንኦተ ሥጋ ምክንያት እንደሚሆንና ደግፎ ሰውን እንደሚያበረታ፣ መንፈሳዊ ምግብ ምሥጢረ ቍርባንም በመንፈሳዊ ነገርና ነፍሳችን በመንፈስ ለመጽናት የበለጠ ይረዳናልና። ጥምቀት ከእግዚአብሔር መወለድ ሲሆን ሜሮን በጸጋ መንፈስ ቅዱስ መጽናት ነው። ሥጋና ደሙን መቀበል ግን ከእግዚአብሔር መዋህድና ተስማሚውን ምግብ መመገብ ነው።ሰውነት የሚጸናው አካልም የሚገዛው፣ በምግብ ስለሆነ፣ክርስቲያኖች ይህንን በመመገባቸው አካለ ነፍሳቸውን ይገዛሉ፤ ሕይወትን ገንዘብ ያደርጋሉ ፤ በጠቅላላው ቍርባን የተፈተነ የሞት መድኀኒት ስለ ሆነ፣ እርሱን የበሉ የሞት ሞት አያገኛቸውም ጌታችን በትምህርቱ እንዳለው ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው።
የቅዱስ ቍርባን ትልቁ ጥቅሙ ዘለዓለማዊ ሕይወት ማግኘት ነው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው ሲል ሕይወት የሆነው ክርስቶስ በቃሉ አስተምሮአል። አንዲት የወይን ቅርንጫፍ ከወይኑ ግንድ ተለይታ ለመኖር
አትችልም ከተለየችም እጣ ፈንታዋ መድረቅ ወይም ሞት ነው። እኛም እንዲሁ ከቁርባን እርቀን፣ ሥጋውና ደሙን ሳንቀበል ብንቀር፣ በራሳችን ሕይወት አይኖረንም። ዮሐ ፲፭፦፩
ይህን ሕይወት የሆነ ስጦታ ለምንቀበል ቅድመ ዝግጅትና ከተቀበሉ በኋላ ድኅረ ጥንቃቄ የሚባሉ ሁለት መረሳት የሌለባቸው ተግባራት አሉ። እነሱም ቅድመ ዝግጅትና ድህረ ጥንቃቄ የሚባሉ፣ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ልንመራባቸው የሚገቡ አበው ያስተማሩን መንፈሳውያን ሕገ ደንቦች ናቸው።
ከቁርባን በፊት ቅድመ ዝግጅት
ሕዝበ ክርስቲያን ቅድመ ቁርባን፣መንፈሳዊና ስጋዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ ቤተክርስትያን ታስተምራለች።
መንፈሳዊ ዝግጅት
+ ንስሐ መግባት፣ እራስን ለካህን ማሳየት (ማስመርመር)፣ ቀኖና ተቀብሎ በሚገባ መፈጸም።
+ ከአበነፍስ (የንስሐ አባት) ጋር ጥልቅና ግልጽ ውይይት ማድረግ
ከመቀበሉ በፊት ግወንድሙ እንዳዘነበት ቢያስብ መባውን ከቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ትቶ አስቀድሞ ሂዶ ከወንድሙ ጋር ይታረቅ ያን ጊዜም መጥቶ መባውን ያቅርብ። እንደተባለ በወንጌል ከቂም፣ ከበቀል፣ከዝሙት፣ከተንኮል፣ከሐሜትና ከመሳሰሉት ነጻ ሆኖ ቢቀበሉት ለድኅነተ ሥጋ ለድኅነተ ነፍስ ይጠቅማል። ለዚህ ነው ካህኑ ዘወትር በቅዳሴ ጊዜ ፍሬ ቅዳሴ ሲደርስ እጁን እየታጠበ፣ ዘኮነ ንጹሐ ይንሣእ እምቍርባን ወዘኢኮነ ንጹሐ ኢያንሣእ ከመ ኢየዐይ በእሳተ መለኮት ዘተደለወ ለሰይጣን ወለመላእክቲሁ ዘቦ ቂም ውስተ ልቡ ወዘቦ ውስቴቱ ሕሊና ነኪር ወዝሙት ኢይቅረብ፣ንጹሕ የሆነ ከቊርባኑ ይቀበል፣ ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል፣ ለሰይጣንና ለመላእክተኞቹ በተዘጋጀ በመለኮት እሳት እንዳይቃጠል። በልቡናው ቂምን የያዘ ልዩ አሳብና ዝሙትም ያለበት ቢኖር አይቅረብ። እጄን ከአፍኣዊ እድፍ ንጹሕ እንዳደረግሁ እንደዚሁ ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ ደፍራችሁ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ብትቀርቡ ከርሱ ለመቀበላችሁ መተላለፍ የለብኝም። ኃጢአታችሁ በራሳችሁ ይመለሳል እንጂ በንጽሕና ሆናችሁ ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ። እያለ ያስጠነቅቃል።ሥርዓተ ቅዳሴ ገጽ ፺፮
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ከመቀበል በፊት፣ እራስን በመመርመር መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ሲናገር፣ በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? ፪ቆረ ፲፫ ፦፭
ወደ ቤተ ክርስቲያን መባዕ ሊያቀርብ ወይም ሊቆርብ ቢወድ በሚገባ ሳይጾም ማንም ሥጋውንና ደሙን አይቀበል። ከወንዶችም ከሴቶችም ወገን የቀመሰ ቢኖር ከዚህም በኋላ ቢቀበል ይህንንም በድፍረት ቢያደርግ ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ይለይ። ሳይገባው የጌታን ሥጋ የበላ፣ ደሙንም የጠጣ፣ በጌታችን ሥጋና በክቡር ደሙ ላይ በደለኛ ነው። ስለዚህ ሰው፣ አስቀድሞ ሰውነቱን መርምሮ ንጹሕ ያድርግ ከዚህ በኋላ ከዚህ እንጀራ ይብላ፣ ከዚህም ወይን ይጠጣ፣ ሳይገባው ከርሱ የበላ የጠጣ የሰውነቱን ጥፋት በላ ጠጣ የጌታችንን ሥጋ አውቆ ከሌላው አለየውምና። ማንም ከመቀበሉ አስቀድሞ ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ራሱን ይመርምር ይልቁንም በጾም ወራት ሃይማኖት ያለው ማንም የሚገድል መርዝ እንኳን ቢሰጠው አንዳች አይጎዳውም። ቆሮ ፲፩፦፳፯ ማቴ ፭፦ ፳፫-፳፬ ፍ.ነ አንቀጽ ፲፫፦፭፻፲፪ ምዕመናንና አበ ነፍሶች በተቻላቸው መጠን ከላይ የተዘረዘሩት መንፈሳዊ ዝግጅት በአትኩሮት ሊጠብቁ ይገባል። ደሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያነጽሐነ እምኩሉ ኃጣውኢነ የሚለውን የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ባለ መረዳት አንዳንድ ካህናት ሳይቀር ሥጋወ ደሙ ለኃጢአት ማስተስሪያ ስለሆነ ዝም ብለው እንዲቆርቡ ሲያደርጉ እናያለን። ነገር ግን የክርስቶስ ሥጋና ደም ያለበቂ ዝግጅት ሲያልፉ ሲያገድሙ የሚቀበሉት አይደለም። ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ለበረከት የሚሆነው፣ በፈሪሀ እግዚአብሔር እራስን በመመርመር ለባርነት እንኳ የማልበቃ ሳለሁ አንተ ግን በልጅነት ክብር አከበርከኝ ለእኔ ስትል በቀራንዮ የተሰዋህ እኔ በደለኛ ነኝና ወደቤቴ ትገባ ዘንድ አይገባኝም በማለት እራስን ዝቅ አድርጎ የበደሉትን ክሶ የቀሙትን መልሶ ሲቀበሉት መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ ይሆንልናል።
ሥጋዊ ዝግጅት
+ ሶስት ቀን ከግብረ ስጋ ግንኙነት መጠበቅ
+ መታጠብ፣ ንጹህ ልብስ መልበስ፣
+ በሚቀበሉበት ዕለት ለአስራ ስምንት ሰዓት መጾም፣
+ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት መገኘትና ማስቀደስ፣
+ ነጠላን መስቀልኛ ማጣፋት
ካህኑ ዝውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ዘመጠዎ በእንተ ኃጣዊኢነ ሲል አሜን ብሎ ሰግዶ መቀበል ያስፈልጋል።አንዳንድ ሰዎች በመስቀል ምልክት ያማትባሉ ነገር ግን አግባብነት የለውም። አሜን ወአሜን ይኩነኒ መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ ብሎ መቀበል እንጂ ማማተብ አያስፈልግም ።
በሚቆርቡበት ቀን የህመም ስሜት፣ መሰናክል ቢያጋጥመን፣ ለምሳሌ ነስር፣ እንቅፋት፣ ትውከት፣ ወደ አፍ የሚገባ ትንኝ፣ ዝንብ… ቢያጋጥመን፤ በዚያን ቀን ሊቆርቡ አይገባም፤
ሕልመ ሌሊት ለሴቶች የወር አበባ(ደመጽጌ) ከታያቸው በዚያን ቀን ሥጋ ወደሙን መቀበልም ሆነ ቤተ ክርስቲያን መግባት ክልክል ነው። መስቀል መሳለም ጸሎት መጸለይ ግን ይፈቀዳል። አንዳአንድ ምዕመናን ደመ ፅጌ(የወር አበባ) ሲታያቸው እራሳቸውን ከጸሎትና ከመባረክ(መስቀል መሳለም) ይለያሉ፣ እንደ ኦሪት ስርዓት አንዲት ሴት ደመ ፅጌ(የወር አበባ/ ካየች እርኩስ ናት። እስክትነጻ ከቤት ውጭ በጥግ ትቆያለች። በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ አስራ አምስት እንደሚገኘው የነካት እንኳ እርኩስ ነበር ስሙ ሳይቀር <መርገም> ይባል ነበር። በሐዲስ ኪዳን ግን መርገም አይደለም። ደመ ፅጌ(የወር አበባ )ይባላል። ርኩሰት የለውም። ነገር ግን ቤተመቅደስ እንዳትገባ የተከለከለችበት ምክንያት የክርስቶስ ደም በሚቀዳበት የሰው ደም ሊነጥብ (ሊፈስበት) ስለማይገባ ነው። ይህ ማለት፣ ካህኑ በራሱ ለቅዳሴ አገልግሎት በሚሄድበት ጊዜ እንደ እንቅፋት፣እሾህ እና የመሳሰሉት ቢያጋጥመውና ቢደማ በዕለቱ ቅዳሴ አይገባም። ደም ስለፈሰሰው ቅዳሴው ይታጎላል ማለት ነው።
ከቁርባን በኋላ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
+ እንደቆረቡ አፍን በነጠላ (ጋቢ) መያዝ ያስፈልጋል
+ ቀጥሎ የቅዳሴ ጸበል መጠጣት፣ የቅዳሴ ጸበል፣የተቀበሉት ሥጋና ደም ከአፋቸውና ከጥርሳቸው ላይ ቀርቶ ወደ ውጪ እንዳይነጥብ ለቃልቆ(ተጉመጥምጦ) ለማውረድ ብቻ ነው። ይህም በቅዳሴ ጸበል ብቻ እንጂ በሌላ ሊፈጽሙት አይገባም
+ አብዝቶ መብላት፣ መጠጣት፣ መነቀስ፣(መበጣት)ደም ቀድቶ ማውጣት አይገባም።
+ ከቆረብን በኋላ ለሁለት ቀን ከግብረ ስጋ ግንኙነት መታቀብ(መከልከል)መራቅ አለብን።
+ ከተቆረበ በኋላ በተለይም ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እንቅፋት(መሰናክል)ቢያጋጥመን ለምሳሌ. ነስር፣ እንቅፋት፣ ትውከት፣ ወደ አፍ የሚገባ ትንኝ፣ ዝንብ ቢያጋጥመን፤ ንስሐ ልንገባና ያጋጠሙንን ችግሮች በሙሉ ለካህን (ለንስሐ አባታችን)ልንናገር ይገባል። የተሰጠንንም ቀኖና ሳንፈጽም ዳግም መቁረብ አይፈቀድም(አይገባም)።
+ ሩቅ መንገድ መሄድ፣ መስገድ፣ አይገባም። ይህም ምስጢሩ፡- ሥጋ ወደሙን የተቀበሉ ሰዎች የዘላለም እረፍት ያገኛሉና በሥጋ ወደሙም ድካም የለበትምና። አንድም በመንግስተ ሰማይ ከገቡ በኋላ ድካም የለምና።
+ ተላምጠው የሚተፉ ነገሮች እንደ ማስቲካ፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የተለያዩ ፍራፍሬና አትክልቶች መብላት አይገባም፡፡
+ ጥፍር መቁረጥ፣ ጸጉር መላጨት፣ ከልብስ መራቆት አይገባም፡፡
ተፈጸመ በረድኤተ እግዚአብሔር ምስጢረ ቍርባን።
ምስጋና ይሁን አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።
መልአከ ሰላም ሰሎሞን ኃይሌ ልዮን ፈረንሳይ
የጽሑፍ አስተያየቶች